AMN- መስከረም 25/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በበርካታ አህጉር ተሻጋሪ ወንዞችና የተፈጥሮ የውኃ ሀብቶች የታደለች ታላቅ ሀገር ናት።
እነዚህን አህጉር ተሻጋሪ ወንዞቿን ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት፣ ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪና ለኃይል ማመንጫነት በስፋት የመጠቀም ሙሉ መብትና አቅምም አላት።
የሀገሪቱን የድህነት ታሪክ ለመቀየርና የህዝቧን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እነዚህን የተፈጥሮ ሀብቶች ለልማት ማዋል አማራጭ የሌለው ወሳኝ እርምጃ ነው።

ከእነዚህ በርካታ ሀብቶች መካከል የዓባይ ወንዝ ዋነኛውና ገናናው ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በወንዙ ላይ የገነባችው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዚሁ ፍትሃዊ የልማት ጥረት ማሳያና የብሔራዊ ኩራት ምልክት ሆኗል።
ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ባለው ሂደት በተፋሰሱ ሀገራት ላይ ምንም ዓይነት አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳላስከተለ በተግባር ተረጋግጧል።
ይልቁንም ግድቡ፣ የውኃ ፍሰቱን በማስተካከል፣ የደለል ክምችትን በመቀነስ እና የጎርፍ አደጋን በመከላከል የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራት የሚጠቅም ዘመናዊ የውኃ መሰረተ ልማት ነው።
ከዚህም በላይ ግድቡ የሚያመነጨው ንጹህ የኤሌክትሪክ ኃይል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣናው ሀገራት ትልቅ እፎይታ እየፈጠረ ይገኛል።
አሁን ላይ ግድቡ የሚያመነጨው ኤሌክትሪክ ለጎረቤት ሀገራት መላክ በመጀመሩ፣ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን የሚያጠናክርና የምስራቅ አፍሪካን የኃይል እጥረት የሚቀርፍ እውነተኛ የጋራ እድገት ማሳያ ሆኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የህዳሴውን ግድብ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፣ ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ የምትጠቀመው የሌሎችን ድርሻ በመጋፋት ወይም ጉዳት ለማድረስ ሳይሆን፣ የራሷን ህዝብ ከጨለማ ለማውጣትና የቀጣናውን ሀገራት በኃይል አስተስስራ በጋራ ለማደግ እንደሆነ አስረግጠው መናገራቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ የታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ፍላጎት እንዲጠበቅና ስጋታቸው እንዲወገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ፍትሃዊ የውኃ አጠቃቀም መርህን በጥብቅ የምትከተል መሆኗንም ገልጸዋል።
ነገር ግን ከዚህ ሁሉ በጎና ፍትሃዊ የልማት እንቅስቃሴ ጀርባ፣ ከተፋሰሱ ሀገራት አንዷ የሆነችው ግብፅ፣ የምትከተለው አካሄድ ፍጹም ግብዝነት የተሞላበት ሆኖ ይስተዋላል።
ግብፅ ለዘመናት የዓባይ ወንዝን በብቸኝነት ስትጠቀም ከመኖሯም በላይ፣ ወንዙን በበረሃማ አካባቢዎች በሚገኙ ክፍት የውኃ ማከማቻዎቿ ላይ በማሳለፍ ከፍተኛ የውኃ ትነትና ብክነት እንዲደርስበት ስታደርግ ቆይታለች።
ይህም ሳያንስ፣ ኢትዮጵያ በገዛ ተፈጥሮአዊ ሀብቷ የመጠቀም መብቷን ተጠቅማ ያስገነባችው ታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ እንዳይካሄድና እንዳይጠናቀቅ በከፍተኛ ቅናትና አላስፈላጊ የፖለቲካ ጫና ስታሴር መቆየቷ ይታወሳል።
ግብፅ አሁንም ቢሆን ዓለም አቀፍ ፍትሃዊ የውኃ አጠቃቀም መርሆዎችን በመጣስ፣ ታሪካዊ ስህተቷን ከማረም ይልቅ ያንኑ መርህ አልባ የሴራ እንቅስቃሴ እና የዲፕሎማሲ ጫና እያስቀጠለች ትገኛለች።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት በእውነትና በፍትሃዊነት ላይ የተመሠረተውን የልማት ጉዞ በፅናት በማስቀጠል፣ የዓባይን ወንዝ ለቀጣናው የጋራ እድገትና ብሩህ ተስፋ የማዋል ሂደታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስምረውበታል።
በታምራት ቢሻው