AMN – ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ቡዜና አልከድር፣ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ብሔራዊ መግባባትን የሚያጠናክርና የአንድነት መንፈስን የሚያድስ መሆኑን ገለጹ።
19ኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችንን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ሃሳብ በከተማ አስተዳደሩ ተከብሯል።
አፈ ጉባዔዋ እንዳሉት፤ የዘንድሮው በዓል መሪ ሃሳብ ሰንደቅ ዓላማ ከምልክትነት ባለፈ ሀገራዊ መግባባትን ለማጎልበት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልፀዋል።

ሰንደቅ ዓላማ የቀድሞ አባቶችና እናቶች በነጻነትና በሉዓላዊነት ለመኖር የከፈሉትን መስዋዕትነት የሚያስታውስ የታሪክ ሕያው ምስክር መሆኑንም ገልጸዋል።
ሰንደቅ ዓላማ በትጋት፣ በጀግንነትና በአንድነት የተገነባች ኢትዮጵያን እንደሚወክል በመግለጽ፤ ሰንደቅ ዓላማን ማክበር ማለት የሀገርን ክብር፣ የሕዝብን ታሪክና የቀጣዩን ትውልድ ተስፋ ማስቀደም መሆኑን አስገንዝበዋል።

ልዩነቶችን በውይይት፣ በምክክርና በሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ የሌላውን አመለካከት ማዳመጥ እንዲሁም ለጋራ ጥቅም በትብብር መሥራት ከሁሉም የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑም ገልፀዋል።
የሰንደቅ ዓላማ ቀን ክብር የሚገለጸው በሚከናወኑ መርኃ ግብሮች ብቻ ሳይሆን ይህን መነሻ በማድረግ በሚወሰደው ቁርጠኝነትና በሚፈጸመው ተግባር ውጤታማነት ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።
ለሀገር ሰላም፣ ደኅንነትና ለሉዓላዊነት መከበር ውድ መስዋዕትነት የከፈሉና አሁንም በዲሲፕሊን ሀገራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ ለሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት፣ የጸጥታ አካላትና ሌሎች የሀገር ባለውለታዎች አመስግነዋል፡፡
በበረከት ጌታቸው