ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን የኢኮኖሚና የፖሊሲ ማዕከልነት በፅኑ መሰረት ላይ እያነጸች ነው

You are currently viewing ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን የኢኮኖሚና የፖሊሲ ማዕከልነት በፅኑ መሰረት ላይ እያነጸች ነው

AMN- ጥቅምት 8/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በህዝቦቿ ጽናትና ህብረት እያሸነፈች፣ ሀገራዊ አንድነቷን፣ የኢኮኖሚ ዕድገቷንና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ተምሳሌትነቷን በፅኑ መሰረት ላይ እያነጸች ትገኛለች።

ይህ አዲስ ሀገራዊና አህጉራዊ ምዕራፍ በተለያዩ ቁልፍ ዘርፎች ስኬቶችን ያስመዘገበ ሲሆን የሀገሪቱን የወደፊት ብሩህ ተስፋና ተደማጭነት በተግባር ያረጋገጠም ሆኗል።

በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች የሕግ የበላይነትን በማስከበር ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና የህዝብ ለህዝብ ወንድማማችነትን ለማጠናከር ሰፊ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያውያንን የነጻነት፣ የጀግንነት፣ የአንድነትና የጋራ መከባበር ታሪክ መሰረት ያደረጉ ሃገራዊ ውይይቶችና ህዝባዊ መድረኮች ብሔራዊ መግባባትንም ይበልጥ እያጠናከሩ ነው፡፡

አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ከተሞች የተከናወነው የኮሪደር ልማት የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ከማሻሻሉም በላይ የከተሞችን ውበትና የቱሪዝም መስህብነት በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል፡፡

በተጨማሪም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል ኤክስፖርት፣ የግብርና ምርታማነትና የፋይናንስ ዘርፍ ማሻሻያዎች ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን የኢኮኖሚ ማዕከልነት በፅኑ መሰረት ላይ አቁመዋል፡፡

በዲፕሎማሲው መስክ ኢትዮጵያ 22 የአፍሪካ ሀገራትን በሚወክለው የዓለም ባንክ ቡድን የአፍሪካ ተወካይ ሆና መመረጧ የአህጉሪቱ ድምፅ የመሆን ተጽዕኖዋን ያሳየ ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ነው።

ከዚህም ባሻገር የብሪክስ አባል መሆኗ፣ የመጀመሪያው የአፍሪካ ወታደራዊ ማርቺንግ ባንዶች ውድድርና ፌስቲቫልን ጨምሮ በርካታ አህጉራዊ ኩነቶችን ለማስተናድ መታጨቷ፣ አዲስ አበባን የአፍሪካ እውነተኛ የዲፕሎማሲና የባህል ማዕከልነቷን ዳግም ያስመሰከረ ሆኗል።

ኢትዮጵያ ያለፉ ስኬቶቿን እያከበረች፣ ፈተናዎችን በጋራ እየተወጣች፣ የበለጸገች ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ በሙሉ አቅሟ እየገሰገሰችም ነው፡፡

የመላው ኢትዮጵያውያን የተቀናጀ ህብረት፣ የመከላከያ ሰራዊት ጀግንነትና የመንግስት ስትራቴጂካዊ አመራር ሀገሪቱን ወደ ላቀ የታሪክ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግራት እሙን ነው።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review