AMN – ጥቅምት 11/2019 ዓ.ም
የታላቁ መደመር ስትራቴጂ በግልጽ እንዳስቀመጠው፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ አስተማማኝ መሠረት በመጣል በአፍሪካ ግንባር ቀደም የብዙዎች ተምሳሌት ትሆናለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ 30 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ የምትተገብራቸውን 7 ግዙፍ ፕሮጀክቶች ማብሰራቸው ይታወሳል፡፡
እነዚህ ሰባቱ የጉባ ብስራት ፕሮጀክቶች፤ የኒውክሌር ማበልጸጊያ፣ በአፍሪካ ግዙፉ አየር ማረፊያ፣ የጋዝ ፋብሪካ ማስመረቅ፣ የነዳጅ ማጣሪያ እውን ማድረግ፣ ሁለተኛውን የጋዝ ፋብሪካ ግንባታ ማስጀመር፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ማስጀመር እና በመላው ሀገሪቱ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ቤቶች ግንባታ ናቸው፡፡
እነዚህ ፕሮጀክቶች ወደ ተግባር የገቡ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ የኒውክሌር ማበልጸጊያ አንዱ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ኮሚሽንን ጎብኝተዋል፡፡

ጉብኝቱን ተከትሎም እንዳገለጹት፤ ኢትዮጵያ እንደ ኒውክሌር ባሉ ዘርፎች ዘግይታ የጀመረች ቢሆንም አሁን ያለችበት ቁመና የሚያኮራ ነው፡፡ ሆኖም ነገ ዓለም በሚወዳደርባቸው በኒውክሌር፣ በስፔስ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት መስኮች ኢትዮጵያን ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገርና ትልቅ ህዝብ ያላት ሀገር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለልጆቻችን አስተማማኝ መሠረት በማስቀመጥ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ እውን የሚሆንበትን መንገድ የመሥራት ኃላፊነት አለብን ብለዋል፡፡
ለትውልድ ማሰብ ተገቢ እንደሆነ የሚያምን ትውልድ እንደሚፈጠር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚሁ ሂደት ውስጥ ሆኖ ኃላፊነት ተሰምቶን ረጅም ጊዜ አቅደንና አስበን ከሠራን፣ እኛ የምንሠራውን ሥራ ልጆቻችን እየገነቡበትና እያበለጸጉበት ይሄዳሉ ብለዋል፡፡
በትዝታ መንግስቱ