AMN- ጥቅምት 22/2019 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ የቦሌ ሹቡ ኤጀርሳ የተቀናጀ የነዋሪዎች መንደርን በደስታ መርቀን ለአካባቢው የልማት ተነሺዎች አስረክበናል ሲሉ ገለጹ።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፀቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ የከተማ ልማት ዋነኛ ዓላማ መሠረተ ልማትን መገንባት ብቻ ሳይሆን፣ የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል፣ መብትና ጥቅም ማስጠበቅ እና የተሻለ የኑሮ ዕድል መፍጠር ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ እየተገነባ የሚገኘው የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ዩኒቨርሲቲ የሀገራችንን የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ እድገት የሚያፋጥን ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ሆኖም ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል መሬቱን ለእርሻ፣ ለግጦሽና ለመኖሪያነት ሲጠቀሙ የነበሩ አርሶ አደሮችን ሕይወት የሚነካ በመሆኑ፣ የልማቱ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ እንዳይሆኑ ልዩ ትኩረት ሰጥተናል ነው ያሉት።
በዚህም መሠረት ለሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ዩኒቨርሲቲ ልማት ከእርሻና መኖሪያ ቦታቸው ተነሺ ለሆኑ የቦሌ ሹቡ ኤጀርሳ አርሶ አደሮች የተቀናጀ መኖሪያ መንደር ገንብተን፣ የኑሮና የገቢ ምንጮቻቸውን የሚያሳድጉ አቅርቦቶችንም አካተናል በማለት ከንቲባዋ ገልጸዋል።
ይህም የነዋሪዎቹን ማኅበራዊ ትስስር ጠብቆ ወደ ተሻለ የአኗኗር ሁኔታ የሚያሸጋግር ሰው ተኮር የልማት አሠራር ነው ሲሉ አክለዋል።

ከመኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ መንደሩ የሚከተሉትን አቅርቦቶች ይዟል፦
* የወተት ላሞችን የሚይዙ የከብት ሼዶችና የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ።
* የንግድ ሱቆች፣ የምርት ማከፋፈያና መሸጫ መጋዘን እንዲሁም ወፍጮዎች።
* የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የሕፃናት መጫወቻና ማቆያ ማዕከል።
* የስብሰባ አዳራሽ።
እነዚህ አቅርቦቶች ነዋሪዎቹ የተሻለ መኖሪያ እንዲኖራቸው፣ የወተት ልማትና ሌሎች የገቢ ምንጮቻቸውን እንዲያሳድጉ፣ ማኅበራዊ ትስስራቸውን እንዲጠብቁ እና ልጆቻቸው ምቹ አካባቢ እንዲያገኙ የተዘጋጁ ናቸው።
ከንቲባ አዳነች በመልዕክታቸው፣ ልማት ማለት ሰውን ከነበረበት ቦታ ማንሳት ብቻ ሳይሆን የኑሮ ደረጃውን ማሻሻል፣ የኢኮኖሚ አቅሙን ማጠናከርና የነገ ተስፋውን ማለምለም ጭምር ነው ብለዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ቦታው ለታላቅ ሀገራዊ ፋይዳ እንደሚውል ስናስረዳቸው፣ ዩኒቨርቲው ለልጆቻቸው የመማር ዕድልና የሀገርን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የመሆን አቅም እንደሚፈጥር በመገንዘብ በፈቃደኝነት ትብብራቸውን አድርገዋል፤ ለዚህ ከልብ እናመሰግናለን፤ ትልቅ ክብርም ይገባቸዋል ነው ያሉት።

ይህ ተግባር በመደመርና በትብብር ስንንቀሳቀስ ሁሉንም ወገኖች ተጠቃሚ ማድረግና ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ እንደምንችል ማሳያ ነው በማለትም አክለዋል።
የቦሌ ሹቡ ኤጀርሳ ነዋሪዎች መንደር ይህንኑ ሰው ተኮር የልማት አቅጣጫችንን በተግባር የሚያሳይ ምሳሌ ነው።
የምንገነባት አዲስ አበባ የሁሉም ነዋሪዎቿን ክብር፣ መብትና ጥቅም የምታስጠብቅ፣ ሁሉንም በእኩል የልማት ተጠቃሚ የምታደርግ ከተማ እንድትሆን ቁርጠኛ ነን ሲሉም አረጋግጠዋል።