አዲስ አበባ፤ የዘላቂ ከተማ ልማት አርአያ

You are currently viewing አዲስ አበባ፤ የዘላቂ ከተማ ልማት አርአያ

AMN- ጥቅምት 22/2019 ዓ.ም

የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ በቅርብ ዓመታት ያስመዘገበችው ፈጣን እና መሠረታዊ ለውጥ፣ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ውብና ጽዱ ዘመናዊ መዲና እንድትሆን አስችሏታል።

የከተማ አስተዳደሩ ሰው ተኮር እና ማህበራዊ ፍትሕን መሠረት ባደረገ የልማት አቅጣጫ የመዲናዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት መሠረታዊ በሆነ መልኩ አሻሽሏል።

ይህ ሁሉን አቀፍ እና የከተማዋ ዘላቂ የልማት እንቅስቃሴ በተባበሩት መንግሥታት UN-Habitat በቻይና በተዘጋጀው የ2026 እ.ኤ.አ የዓለም ከተሞች ቀን “የሸንሃይ አዋርድ” ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንድትጎናጸፍ አድርጓታል።

የከተማዋ የኮሪደር እና የወንዝዳርቻ ልማት ፤ የኢኮኖሚና የቱሪዝም አቅምን በማጎልበት ብቻ ሳይወሰን የዜጎችን መኖሪያ እና ኑሮ በተግባር ያሻሻለ ነው፡፡

ቀደም ሲል የሰውን ልጅ ክብር በማይመጥኑ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ነዋሪዎች በዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ተጠቃሚ በመሆናቸው ማህበራዊ ክብራቸው ከፍ ብሏል።

በተመሳሳይ የወንዝ ዳርቻዎች ከነበሩበት የብክለት እና የደህንነት ስጋት ወጥተው ለአካባቢ ጥበቃ እና ለህዝብ ማረፊያ ምቹ ቦታዎች ሆነው ተደራጅተዋል።

በከተማ ልማቱ ለሕጻናት የመጫዎቻና መዋያ ስፍራዎች፣ ለወጣቶች ደግሞ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያዎችና ፓርኮች በመገንባታቸው ከተማዋ ለስፖርት ቱሪዝምና ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ተመራጭ ሆናለች።ከተማዋ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት ከማስገባት በተጨማሪ ዘመናዊ ተርሚናሎችን፣ የመኪና ማቆሚያዎችን እና የቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎችን በጥራት በመገንባት የትራንስፖርት አገልግሎቷን አዘምናለች።

እንዲሁም በደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ የተወሰዱ ፈጣን እርምጃ ከተማዋን ውብ እና ጤናማ አድርጓታል።

ለከተማ ውበት፣ ለካርቦን መቀነስ እና ለአካባቢ ጥበቃ ወሳኝ የሆኑ ችግኞች በስፋት መተከላቸውም ሌላኛው አዲስ አበባን ከብክለት የጸዳች አረንጓዴ መዲና ካደረጓት መካከል ተጠቃሽ ነው።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተፈጠረው አዲሱ የ24/7 የሥራ ባህል ውጤት የሆነው ይህ ዕድገት፣ አዲስ አበባን ለአፍሪካና ለሌሎች ዓለም አቀፍ ከተሞች ተምሳሌት አድርጓታል።

በትዝታ መንግስቱ

#ትልቅሃገር#ትልቅህዝብ#ታላቅርዕይ#አዲስሚዲያኔትዎርክ#የትዉልድድምጽ#አዲስአበባ#ኢትዮጵያ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review