በመቐለ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በፍጥነት ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው

You are currently viewing በመቐለ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በፍጥነት ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው

AMN- ጥቅምት 23/2019 ዓ.ም

በመቐለ ከተማ “የመሶብ” የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በፍጥነት ለማስጀመርና የህዝብን ዕለት ተዕለት ፍላጎት በዘመናዊ መልኩ ለማሟላት የሚያስችል ውይይት ተካሄደ።

በመቐለ ከተማ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በፍጥነት ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን የመቐለ ከተማ ከንቲባ ሺሻይ አማረ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

የፌደራል የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አመራሮችና ሙያተኞች መቐለ ከተማ በመገኘት አገልግሎቱን እውን ለማድረግ ከከተማዋ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ጋር የተመካከሩ ሲሆን፣ ይህ እርምጃ በትግራይ ክልል የተጀመረውን የሰላም ተስፋና ሀገራዊ የልማት ትስስር በተግባር ያረጋገጠ ምዕራፍ ሆኗል።

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የፌደራል የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዮናስ አለማየሁ፣ አሁን ላይ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተዋል።

በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት 114 አገልግሎቶችን በአንድ ጣሪያ ሥር መስጠት የተቻለበት ደረጃ ላይ በመደረሱ፣ የዜጎች እርካታ 99 በመቶ መድረሱንም ጠቅሰዋል።

አሰራሩ በሁሉም ክልሎች በስፋት እየተተገበረ የሚገኝ ቢሆንም፣ በነበረው ነባራዊ ሁኔታ በትግራይ ክልል እስካሁን ሳይጀምር ቆይቷል። ይሁን እንጂ አሁን ላይ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አገልግሎቱን ለማስጀመር ያሳየውን ቁርጠኝነት ዋና ሥራ አስፈፃሚው አድንቀዋል።

የመቐለ ከተማ ከንቲባ ሺሻይ አማረ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በሌሎች አካባቢዎች የታየው ፈጣንና ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ በመቐለ ከተማም በፍጥነት እንዲጀምር በትኩረት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የታየው የፈጣን አገልግሎት አሰጣጥ ተሞክሮ በትግራይ ክልልም በፍጥነት ሊተገበር እንደሚገባ ያነሱት ከንቲባው፣ የፌደራል የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች፣ ሥልጠና በመስጠትና የዕውቀት ሽግግር በማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም በመቐለ ከተማ የሚከናወነው ሥራ በሌሎች የትግራይ ክልል አካባቢዎች ለሚገነቡ ማዕከላት እንደ መነሻ የሚያገለግል በመሆኑ፣ ሥራው በፍጥነት፣ በጥራትና በትኩረት ሊከናወን እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review