መንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ምህዳሩን ምቹ የሚያደርጉ ውጤታማ ተግባራት አከናውኗል

You are currently viewing መንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ምህዳሩን ምቹ የሚያደርጉ ውጤታማ ተግባራት አከናውኗል

AMN- ጥቅምት 23/2019 ዓ.ም

መንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ምህዳሩን ምቹ የሚያደርጉ ውጤታማ ተግባራት ማከናወኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ ገለጹ።

አልጀዚራ ሚዲያ ኔትወርክ የተመሰረተበትን 30ኛ ዓመት አክብሯል።

በበዓሉ አከባበር ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አምባሳደሮች፣ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎችና ባለሙያዎችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ መንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ምህዳሩን ምቹ የሚያደርጉ ውጤታማ ተግባራትን አከናውኗል።

የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ተደራሽ ከማድረግ ጀምሮ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ አሰራሮችና የፖሊሲ እርምጃዎችን መውሰዱንም አንስተዋል።

ይህ የለውጥ እርምጃ የውጭ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አመልክተው፣ አልጀዚራ ሚዲያ ኔትወርክም የዚህ ለውጥ ፍሬ ተቋዳሽ ነው ብለዋል።

አልጀዚራ በተለያዩ መስኮች በኢትዮጵያ ሽፋን በመስጠት የሚያበረታታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይ የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግንዛቤው እንዲሰፋ የሰራው ስራ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው ብለዋል።

የአልጀዚራ ሚዲያ ለኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞች አቅም ግንባታ ስልጠናዎች በመስጠት፣ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የሙያ ደረጃ እንዲያድግ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

አልጀዚራ ሚዲያ በኢትዮጵያ ያሉ ታሪካዊ መስህብ ቦታዎች፣ የተፈጥሮ ሀብት እና የኢኮኖሚ ዕድሎችን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስተወወቅ ላይ የጀመረውን ስራ ሊያጠናክር እንደሚገባም ነው ዋና ዳይሬክተሯ ያስገነዘቡት።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን በኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙሃን ጋር ገንቢ የሆነ ትብብሩን እንደሚያጠናክርም አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ-መንበር አምባሳደር ሳልማ ሀዳዲ በበኩላቸው፣ አፍሪካ ብዝሃነት፣ ትልቅ ዕድልና ማህበራዊ ተልዕኮ ያላት አህጉር መሆኗን አስታውሰዋል።

ለዚህም የአፍሪካ ተቋማት ስኬቶች፣ እርምጃዎችና ህዝቦቿ ሙሉ ትኩረት ይፈልጋሉ ነው ያሉት።

አፍሪካ የምትጠይቀው ወገንተኛ ዘገባ እንዲሰራላት አይደለም ያሉት አምባሳደር ሳልማ፣ ለአፍሪካውያን ድምፅ፤ ስለ አህጉሪቱ አጠቃላይ መጻኢ እድል በሚደረጉ ውይይቶች ውስጥ ተገቢውን ቦታ የሚሰጥ ትክክለኛ፣ ፍትሃዊ እና ሁኔታዎችን ያገናዘበ ዘገባ እንዲቀርብ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የአልጀዚራ ሚዲያ ኔትወርክ የኢትዮጵያ ቢሮ ኃላፊ መሀመድ ተወከል በበኩላቸው፣ ሚዲያው በኢትዮጵያ ከምስረታው ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት ላደረጉት ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል።

ሚዲያው ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ መሆን የሚለውን መርህ በመከተል በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸው፣ አሁን ላይ ሚዲያው የሚያሰራጭበትን ቻናል ወደ ሦስት ከፍ ማድረጉን አብራርተዋል።

አልጀዚራ ሚዲያ ኔትወርክ አብረው ለሰሩ የመንግሥት ተቋማት፣ አህጉራዊ ድርጅቶችን ጨምሮ ለተለያዩ አካላት እውቅና መስጠቱን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review