AMN – ጥቅምት 23/2019 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ያላትን ግዙፍ የታዳሽ እና የአማራጭ ኢነርጂ ሀብት በተቀናጀ መልኩ በመጠቀም የኢኮኖሚ ዕድገቷን ከማፋጠን ባለፈ፣ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለቀጣናዊ የኃይል ትስስር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተች ትገኛለች።
በውኃ፣ በንፋስ፣ በፀሐይ እና በምድር በእንፋሎት (ጂኦተርማል) ሀብቷ የምትታወቀው ኢትዮጵያ፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በርካታ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን እውን አድርጋለች።
እነዚህ የኃይል ምንጮች ለኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ለአምራች ዘርፎች አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት በመፍጠር የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ሽግግር እየደገፉ ይገኛሉ።
የኃይል ዘርፍ ልማቱም ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባሻገር ለጎረቤት ሀገራት ኤሌክትሪክ በመሸጥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ላይ ይገኛል።
ቀደም ሲል ለቤት ውስጥ አገልግሎት ይውል የነበረውን የእንጨት ፍጆታ በንጹህ ኢነርጂ በመተካት የደን ጭፍጨፋን ለመቀነስ እና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ውጤታማ ለማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሚያደርገው ርብርብ የንጹህ ኢነርጂ ሚና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
በተለይም አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የምታበረክተው አስተዋጽኦ አነስተኛ ቢሆንም፣ እንደ ድርቅ፣ ያልተጠበቀ ዝናብ፣ ጎርፍ እና ከፍተኛ ሙቀት ያሉ አደጋዎች በአህጉሪቱ በሚኖሩ ዜጎች ሕይወት ላይ ፈተና ሲሆኑ ይስተዋላል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም (ንጹህ) የኢኮኖሚ ስትራቴጂ በመንደፍ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች።
ስትራቴጂው የከሰል እና የእንጨት አጠቃቀም የሚያስከትለውን የአየር ብክለትና ተያያዥ የጤና ችግሮች በእጅጉ እየቀነሰ ይገኛል።
ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማትን በማስፋፋት በቀጣናው የንጹህ ኃይል ማዕከል በመሆን ለጎረቤት ሀገራት ኤሌክትሪክ በማቅረብ ቀጣናዊ ትብብርና ትስስርን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተች ትገኛለች።
በበረከት ጌታቸው