AMN – ጥቅምት 25/2019 ዓ.ም
ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት በጽኑ መሰረት ላይ ለመገንባት የሚያስችል ሀገራዊ መግባባት መፍጠር የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካ ፕሮግራም ዋነኛ ግብ ነው፡፡
ዲሞክራሲ የበለጸገችና ህብረ ብሄራዊ አንድነቷ የተረጋገጠ ኢትዮጲያን ለመገንባት ቁልፍ መሆኑንም ፓርቲው ያምናል፡፡
እነዚህን ሀገራዊ ግቦች ለማሳካት የሚደረገው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከአህጉራዊ አጋሮች ጋር ያለውን ትብብርም ለማጠናከር ፓርቲው እየሰራ ይገኛል። በዚህም ሁለተኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ከጥቅምት 26 እስከ 28 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል። የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ፖሊሲ አውጪዎች እና በተለያዩ ዘርፎች ተወካዮች ጨምሮ በርካታ ተሳታፊዎች ይታደማሉ፡፡
በጉባዔው የአፍሪካን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ የወደፊት አቅጣጫዎች የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ምክክር ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል። ይሄም የፓርቲ-ለፓርቲ ግንኙነትን ለማጠናከር እና ከቀጣናውና ከአፍሪካ ፓርቲዎች ጋር የሁለትዮሽ እና የባለ ብዙ ወገን ውይይት ለማድረግ ሰፊ እድል ይፈጥራል፡፡
ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድንና በዲጂታል ዘርፎች ያስመዘገበቻቸውን ውጤታማ ተሞክሮዎች በጉባኤው እንደምታቀርብም ይጠበቃል።
በዚህም በሃይል፣ በትራንስፖርት፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እና በአረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ ያገኘችውን ልምድ ለአፍሪካ ማካፈል እና የጋራ ትስስር መፍጠርም ያስፈልጋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ንግድን፣ ኢንቨስትመንትንና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያሳልጡ ህጎች በየሀገራቱ እንዲፀድቁ ማድረግ እንዳለባቸው ይገለጻል፡፡

የዲፕሎማሲ ማዕከል በሆነችው አዲስ አበባ የሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ፤ለከተማዋ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያስገኝላታል፡፡ የአዲስ አበባን በጎ ገጽታ ለአፍሪካ መሪዎች ከማሳየት በተጨማሪ የከተማዋን ኢኮኖሚ እንዲነቃቃም ያደርጋል፡፡
ጉባኤው ለአዲስ አበባ በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ዘርፈ ብዙ ስኬት ያስገኛል፡፡ አዲስ አበባ ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ያስተናገደች ሲሆን በተያዘው በጀት ዓመትም በርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በስኬት እያስተናገደች ትገኛለች።
ለዚህም አዲስ አበባ እንደ አፍሪካ መዲናነቷ ጉባዔውን ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃለች፡፡
የሻምበል ምህረት