AMN- ጥቅምት 25/2019 ዓ.ም
ብልጽግና ፓርቲ ላለፉት ዓመታት ያከናወናቸውን ሁለገብ ሥራዎች እና ያስመዘገባቸውን ድሎች መሠረት በማድረግ፣ በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተወዳጅነት እና ቅቡልነት በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።
ፓርቲው የገባውን ቃል በተግባር በመፈጸም ያስመዘገበው ውጤት፣ በአፍሪካ ደረጃ ለሚገኙ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር አርዓያ ሊሆን የሚችል ታሪካዊ ምዕራፍ ከፍቷል።
አንድ ፓርቲ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን ሊያጎናጽፈው የሚችለው የገባውን ቃል በዕውን ሲያሳይ ነው።
ብልጽግና ፓርቲ በምርጫ ወቅት የገባቸውን ቃል ኪዳኖች በልማት፣ በሰላም እና በዴሞክራሲ ግንባታ መስኮች በመሬት ላይ በማውረድ የላቀ አርአያነት አሳይቷል። በተለይም በፈተናዎች ውስጥም ጭምር ቃልን ከትግባር ጋር በማቀናጀት ያሳየው ቁርጠኝነት ለአህጉሪቱ ፓርቲዎች የፖለቲካ ጽናት ማሳያ ሆኗል። የፓርቲው ታታሪነት እና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ ፖሊሲ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን አስገኝቶለታል።
ይህንን ተከትሎም በነጻ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ ሕዝቡ ለፓርቲው ድምፅን በመስጠት ዳግም እንዲመረጥ አድርጎታል። ይህ ድል የሕዝቡን አደራ በታማኝነት ለመወጣት የተከፈለው መስዋዕትነት ውጤት ነው።
በምርጫ የተገኘው ዳግም ዕድል ፓርቲው የጀመራቸውን ሀገራዊ የለውጥ እና የልማት ጉዞዎች አጠናክሮ ለማስቀጠል ትልቅ መሠረት ጥሏል፡፡ በበጋ ስንዴ ልማት እና በሌሎች ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ሀገሪቷን በምግብ ራስን ወደ መቻል ለማሸጋገር ስኬታማ ጥረቶች ተደርገዋል።
የኢትዮጵያን ብርሃን የማረጋገጥ እና ለአፍሪካ ቀጣና የኤሌክትሪክ ኃይል የማዳረስ ታላላቅ ፕሮጀክቶች መሳካት ችለዋል። የከተሞችን ገጽታ በመቀየር ለኑሮ ምቹ እና ለቱሪዝም ሳቢ የሆኑ ዘመናዊ መዋቅሮችን በመገንባት አመርቂ ስኬቶች ተመዝግበዋል።

በአጠቃላይ፣ የብልጽግና ፓርቲ ጉዞ ቃሉን ከግብ በማድረስ፣ ሕዝባዊ ቅቡልነትን በማረጋገጥ እና የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ በሚደረገው ርብርብ አበረታች አርዓያነትን ይዞ የሚቀጥል መሆኑን አሳይቷል።
ፓርቲው ባሳያቸው አመርቂ ውጤቶች እና ባስመዘገባቸው ስኬቶች የተነሳ 2ኛውን የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ እንዲያዘጋጅ መመረጥ ችሏል፡፡
ከነገ ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው በዚህ ታላቅ ጉባኤም እነዚህንና ሌሎች ህዝብ እና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የመሰከረላቸው ስኬቶቹን በተሞክሮነት ያጋራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በታምራት ቢሻው