AMN- ጥቅምት 27/2019 ዓ.ም
አዲስ አበባ ከተማ በፈጣን የከተማ መሠረተ ልማት እና ዕድገት አስደናቂ ውጤት በማስመዝገብ የዓለም ከተሞች ተወዳዳሪ እየሆነች ትገኛለች።
መዲናዋ ሁለተኛውን የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ እያስተናገደች ሲሆን የጉባኤው ተሳታፊዎች በከተማዋ የተመዘገበውን ሁለንተናዊ ለውጥ በአካል በመጎብኘት ያዩትን አድናቆት ለኤ ኤም ኤን ገልጸዋል።
የጉባኤው ታዳሚዎች እንደገለጹት፤ መዲናዋ መሠረተ ልማቶችን በፍጥነት እና በጥራት ከማጠናቀቅ ባለፈ የአገልግሎት እንግልትን እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የዘረጋችው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥርዓት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ተሞክሮ የሚሆን ነው።
ከተማዋን ከዚህ በፊት ያውቋት የነበሩት የጉባዔው ተሳታፊዎች፤ በወቅቱ ያዩትን እና የዛሬውን ሁለንተናዊ ለውጥ ሲያነጻጽሩ የተሰማቸውን ግርምትና አድናቆት አብራርተዋል።
በከተማዋ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማትና የማስዋብ ሥራ፣ ወንዞችን ከብክለት የመታደግና የማጽዳት እንቅስቃሴ እንዲሁም ሃብቶችን እንደገና ጥቅም ላይ የማዋል ሂደት አስደናቂ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህም በመንግሥት ራዕይ፣ ጥናትና ቁርጠኝነት የተመራ የቅንጅት ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የመዘመን እና ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘመን የመሸጋገር ጉዞ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በምሳሌነት ሊወሰድ እንደሚገባው የጉባዔው ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
በተጨማሪም የከተማዋ ውበት፣ የሕዝቡ እንግዳ ተቀባይነት እንዲሁም የመሠረተ ልማት አቅርቦቱ ፍጹም አስደናቂ መሆኑን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ መለወጥና መዘመን ከፍተኛ ደስታ የተሰማቸው የጉባኤው ታዳሚዎች፤ ሌሎች የአህጉሪቱ ዜጎችም አዲስ አበባ እና በምድር ቀደምቷ ኢትዮጵያ የጉዞ መዳረሻቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በትዝታ መንግስቱ
#ትልቅሃገር#ትልቅህዝብ#ታላቅርዕይ#አዲስሚዲያኔትዎርክ#የትዉልድድምጽ#አዲስአበባ#ኢትዮጵያ#የአፍሪካፖለቲካፓርቲዎችጉባኤ