AMN – ግንቦት 19/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ዕድገትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች እኩል ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት በቦረና ዞን የተገነባውን የነገሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያን መርቀው ሥራ ባስጀመሩበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ነው።
የቦረና ሕዝብ የኦሮሞን ማንነትና ባሕል ያቆየ፣ ከአጎራባች የጉጂ እና የባሌ ሕዝቦች ጋር በትብብርና በሰላም የኖረ ታላቅ ሕዝብ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አካባቢው ከአዲስ አበባ የራቀ ከመሆኑ አንጻር የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማት መገንባቱ እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚ ሥራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያንና የወታደራዊ አየር ኃይል ጣቢያዎችን ጨምሮ ወደ 30 የሚጠጉ አውሮፕላን ማረፊያዎች እንዳሉ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ እነዚህ መሠረተ ልማቶች በክልሎች መካከል ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሊጣጣሙ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በአሁኑ ወቅት በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል 10፣ በምዕራብ 7፣ በደቡብ 6 እንዲሁም በምስራቅ 5 አውሮፕላን ማረፊያዎች እንደሚገኙም በዝርዝር አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያከናወነ ያለውን ሥራ ያደነቁ ሲሆን፤ በቀጣይም በምስራቅና በደቡብ ኢትዮጵያ ሊሟሉ የሚገባቸውን ተጨማሪ መዳረሻዎች በመለየት ሥራዎች እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡

በተለይም ግንባታው የተጀመረው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሙሉ መልክ ሲይዝ፤ የጎደሉ ቦታዎችን ከመንግሥት ጋር በመመካከር በዕቅድ መሙላት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ “ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ነገር ለዜጎች እኩል ተደራሽ እንዲሆን፣ ፍትሐዊነትንና እኩልነትን ለማረጋገጥ የጎደሉ ነገሮችን እያዩ መሄድ ያስፈልጋል” ብለዋል።

ለቦረና እና ለጉጂ ሕዝቦች ባስተላለፉት መልዕክት፤ ብንዘገይም እየደረስን ነው፤ ሕዝቡ የሰላም ዓምድ በመሆኑ፣ ይህ የሰላምና የልማት ጉዞ ተባብሮ ሀገርን ለማጽናት እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በወርቅነህ አቢዮ