ብልፅግና ፓርቲ የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭን በበላይነት እንዲመራ ተመረጠ

You are currently viewing ብልፅግና ፓርቲ የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭን በበላይነት እንዲመራ ተመረጠ

AMN- ጥቅምት 28/2019 ዓ.ም

ብልፅግና ፓርቲ የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭን (APPI) በበላይነት እንዲመራ በሙሉ ድምጽ ተመርጧል።

የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ኢኒሼቲቩን እንዲመሩ ዋና ጸሐፊ በመሆን ተሾመዋል።

ሶስተኛ ቀኑን የያዘውና በዓድዋ ድል መታሰቢያ “ዕድገትን መምራት ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሔደ የሚገኘው 2ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በጉባኤው ላይ ብልፅግና ፓርቲ የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተነሳሽነትን (APPI) በበላይነት እንዲመራ በሙሉ ድምፅ የተመረጠ ሲሆን ይህም የፓርቲውን አህጉራዊ ተሳትፎ እና እውቅና የሚያጎላ ትልቅ ምዕራፍ ነው።

ውሳኔው የተላለፈው ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተወከሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና ተወካዮች ባደረጉት ጥልቅ ውይይት ነው።

በውይይቱም የብልፅግና ፓርቲ በሃገር ግንባታ፣ በኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን እና በመደመር ፍልስፍና ዙሪያ ያለው ተሞክሮ ጎልቶ ተነስቷል።

ተሳታፊዎቹ ይህ የብልጽግና ፓርቲ ልምድ ለመላው አፍሪካ ፓርቲዎችና ሀገራት መልካም ተሞክሮ ሊወሰድበት የሚችል መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭ (APPI) የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች በተግባር የመተርጎም ኃላፊነት የተጣለበት የበላይ አስፈጻሚ አካል ነው።

የኢኒሼቲቩ ዋና ስትራቴጂክ ተልዕኮ የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ማካሄጃ መሳሪያዎች ብቻ ከመሆን ተሻግረው ለፖሊሲ ዝግጅት፣ ለመልካም አስተዳደር፣ ለአመራር ልማትና ለኢኮኖሚ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ጠንካራና ዘላቂ ተቋማት እንዲሆኑ ማብቃት ነው።

ይህ ክስተት ለብልጽግና ፓርቲም ሆነ ለኢትዮጵያ ትልቅ አህጉራዊ እውቅናን የሚያጎናጽፍ ሲሆን የአገሪቱን የልማት ተሞክሮ እንዲሁም በመደመር ፍልስፍና ላይ የተመሰረተውን የሀገረ መንግስት ግንባታ ራዕይ ወደ አፍሪካ ተቋማዊና ፖለቲካዊ መድረክ እንዲመጣ አድርጎታል።

ከመላው አፍሪካ የተውጣጡ ተወካዮች በኢትዮጵያ የልማት ተሞክሮና ብልጽግና ፓርቲ ለሀገሪቱ ትራንስፎርሜሽን እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ በአጽንኦት አንስተዋል።

የጉባኤውን ውጤቶች የያዘው የአዲስ አበባ ድንጋጌ (Addis Ababa Declaration) ዛሬ ይፋ ይደረጋል ተብሎም ይጠበቃል።

ይህ ጉባኤ በብልጽግና ፓርቲ አህጉራዊ ተሳትፎ ውስጥ ጉልህ ምዕራፍ የሚከፍት፣ የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ እውቅና የሚያጎናጽፍ፣ እንዲሁም ለጠንካራ ፖለቲካዊ ተቋማት ግንባታ፣ ለጋራ ትብብርና ለአፍሪካ ብልጽግና ያለውን ቁርጠኝነት ዳግም ያረጋገጠ መሆኑን ከፓርቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡።

#ትልቅሃገር#ትልቅህዝብ#ታላቅርዕይ#አዲስሚዲያኔትዎርክ#የትዉልድድምጽ#አዲስአበባ#ኢትዮጵያ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review