ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የጋራ ብልፅግና ጠንካራ መሠረት እየጣለች ነው

AMN- ነሐሴ 6/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትስስርንና አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደትን በማፋጠን ለአፍሪካ የጋራ ብልፅግና ጠንካራ መሠረት እየጣለች መሆኗን በኢትዮጵያ የዛምቢያ አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ ገለጹ።

ዛምቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ብዝኅ ዘርፍ የዲፕሎማሲ ትብብር በአዳዲስ መስኮች ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ ፤ ኢትዮጵያ በቀጣናዊ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ በመሠረተ ልማት ትስስር፣ በንግድና ኢንቨስትመንት የትብብር መስኮች የፈጠረችው የልማት አቅም ተምሳሌታዊ መሆኑን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያና ዛምቢያ መካከል የተቋቋመው የጋራ ትብብር ኮሚሽንም ቀጣይ ስብሰባውን በኢትዮጵያ በማካሄድ የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያስገኙ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ስብሰባውም በሁለቱ ሀገራት መካከል በተለያዩ ዘርፎች እየተካሄዱ ያሉ የትብብር ሥራዎችን ለመገምገምና ወደፊት የሚወሰዱ አዳዲስ የትብብር አቅጣጫዎችን ለመወሰን ወሳኝ እንደሚሆን ገልጸዋል።

በንግድ፣ ዲጂታላይዜሽን፣ ሥልጠናና በአቪዬሽን ዘርፍ የትብብር ዕድሎችን በመለየት የሀገራቱን ግንኙነት ወደ ተጨባጭ የጋራ ጥቅም ለመቀየር የሚያስችል ዕቅድ እየተዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ዛምቢያና ኢትዮጵያ በምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (COMESA) ከሁለቱ ሀገራት ጥቅም ባሻገር የአፍሪካን የጋራ ድምፅ በዓለም አቀፍ መድረክ ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም የኢትዮጵያና ዛምቢያ ግንኙነት ከታሪካዊ የዲፕሎማሲ ትብብር የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያጎለብት ሁለንተናዊ አጋርነት እየተሸጋገረ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የደን መልሶ ማልማትን በማጠናከር ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታና ለዘላቂ ልማት በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኗን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በትክክለኛ የዕድገት አቅጣጫ እየተንቀሳቀሰች ነው ያሉት አምባሳደር ሙቻንጋ፤ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ግንባታ እመርታዎቿም ለሌሎች የዓለም ሀገራት ጭምር አርአያ ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአህጉራዊ ትስስርና በአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች የመሪነት ሚና እየተወጣች መሆኑን ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

በዚህም በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) እና በምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) በንቃት እየተሳተፈች እንደምትገኝም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ማዕቀፍ የንግድ ልውውጥን ለማቀላጠፍ እየሠራች መሆኑንም አስረድተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review