የሰንበት ገበያዎች የኑሮ ውድነትን እያቃለሉ ነው

AMN – ጥቅምት 29/2019 ዓ.ም

ከተማን ማልማት ከታላላቅ ሕንጻዎችና አስፋልት መንገዶች ባሻገር የነዋሪዎችን ኑሮ ማሻሻል ላይ ማተኮር መሆኑን የተረዳው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ የኑሮ ውድነትን ለማስታገስ የዘረጋቸው 282 የሰንበት ገበያዎች በነዋሪዎች ሕይወት ላይ አዎንታዊ ለውጥ እያመጡ ይገኛሉ።

ባለፉት አምስት ዓመታት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑት ሰው ተኮር ሥራዎች በነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ተጨባጭ ለውጥን ፈጥረዋል።

በተለይም በመዲናዋ የሚስተዋለውን የኑሮ ጫና ለማቅለል በአምስቱም የከተማዋ መግቢያ በሮች ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት መገንባታቸው እና ከ282 በላይ የሚሆኑ የሰንበት ገበያዎች ወደ ሥራ መገንባታቸው ለሸማቹ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ናቸው፡፡

እነዚህ የሰንበት ገበያዎች ሕብረተሰቡ በአቅራቢያው ጥራት ያላቸው ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ነው።

በገበያ ማዕከላቱ የተዘረጋው አሠራር ምርቶች ከአምራቹ ቀጥታ ወደ ሸማቹ እንዲደርሱ በማድረግ፣ ሕገ-ወጥና አላስፈላጊ የዋጋ ንረትን ማስቀረት ችሏል።

እንዲሁም በኬላዎች ላይ የሚታዩ ጫናዎችን በማስወገድ አርሶ አደሩና ሸማቹ በቀጥታ እንዲገናኙ ምቹ ዕድል ተፈጥሯል።

እነዚህ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላትና የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች አዲስ አበባን ከአጎራባች አካባቢዎች ጋር በንግድ በማስተሳሰር ረገድ ያላቸው ሚና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መጥቷል።

የተለያዩ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች የሸማቹን ኪስ በማይጎዳ መልኩ እንዲቀርቡ በማድረግ፣ አርሶ አደሩን ከከተማው ሸማች ጋር በቀጥታ በማገናኘት በመሃል የሚገቡ ደላሎችን ከግብይት ውጪ ማድረግ ተችሏል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review