የህብረት ስራ ማህበራትን በማጠናከር የፋይናንስ አቅምን ማሳደግ ተችሏል

You are currently viewing የህብረት ስራ ማህበራትን በማጠናከር የፋይናንስ አቅምን ማሳደግ ተችሏል

AMN ሕዳር 1/ 2019 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ህብረት ስራ ማህበራት ኮሚሽን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ78ኛ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ35ኛ ጊዜ የሚከበረውን የቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ቀን አከባበር እና የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ ህብረት ስራ ማህበራት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተጫነ አዱኛ፤ የህብረት ስራ ማህበራት ከተቋቋሙበት ጊዜ አንስቶ አባላት የቁጠባ ባህላቸውን አጎልብተው ችግሮቻቸውን የሚፈቱበትን ዕድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሁን ላይ ሁለት የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ዩኒየኖች የሚገኙ ሲሆን፣ ከ291 ሺህ በላይ አባላትን አቅፈው ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ጠቅላላ ሀብት ማፍራት ችለዋልም ብለዋል።

የህብረት ስራ ማህበራትን በማጠናከር የፋይናንስ አቅማችንን ማሳደግ ችለናል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ በዚህም ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ቁጠባ ማሰባሰብ መቻሉን አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ78ኛ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ35ኛ ጊዜ የቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ቀንን እነዚህን ውጤቶች በሚመጥን መልኩ እንደሚያከብር ገልጿል።

ዕለቱ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሚከበር ሲሆን፤ የማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ህዳር 3 ቀን 2019 ዓ/ም የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን በማቅረብ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመገምገም እና በውይይት እንደሚከበር ተጠቁሟል።

በራሄል አበበ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review