AMN ኅዳር 01/2019 ዓ.ም
በዋግ ህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ራሱን አዴን ብሎ የሚጠራው ቡድን 270 ታጣቂዎች መንግሥት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ በመቀበል ለመከላከያ ሠራዊት እጅ ሰጥተዋል።
በቀጣናው የሚገኘው ኮር ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል መለሰ ሙሉ በግጭትና ጫካ በመግባት ወይንም አላሥፈላጊ ሁከት በመፍጠር የሚፈታ ችግር አለመኖሩን አውቃችሁና ሠላም መርጣችሁ በመምጣታችሁ ህብረተሰቡም ሆነ የአካባቢዉ ሽማግሌዎች ደስተኞች ናቸው ሲሉ ገልፀዋል።
የዋግ ህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሚሊሺያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮሚሽነር አበበ ተክሌ በበኩላቸዉ በዞኑ በርካታ ታጣቂዎች ወደ ሠላማዊ ሕይወት እየተመለሱ መሆኑን ተናግረዋል።
የመንግሥት የሰላም ጥሪ ውጤቱ ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው ፤ የታጣቂዎች መመለስ ሰላምን ከማረጋጋት በተጨማሪ በጋራ ሆኖ የማኅበረሰቡ የልማት ጥያቄዎች እንዲመለሱ ዕድል እንደሚኖረውም ገልፀዋል።
በተሣሣተ መንገድ ወደ ጫካ ገብተው መቆየታቸውን የገለፁት የአዴን ታጣቂዎቹ ፤እስካሁን ካደረስነው ጥፋታችን ተምረን ለዘላቂ ሰላም መምጣት የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ ተናግረዋል።
የታጣቂዎቹ ወደ ሰላም መምጣት የአካባቢው ሰላም እንዲረጋገጥና አብሮነት እንዲጎለብት ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም ገልፀዋል። የቀሩት ታጣቂዎች ወደ ሰላም እንዲመለሱ ቀጣይነት ያለው ስራ እንደሚሠሩ ማስረዳታቸዉን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ኦንላይን ሚዲያ መረጃ ያመላክታል፡፡