ከመላዉ ዓለም ለCOP32 ጉባኤ ምድረ ቀደምት ሀገር ወደሆነችው ኢትዮጵያ የሚመጡ ተሳታፊዎችን ለመቀበል ዝግጁ ነን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing ከመላዉ ዓለም ለCOP32 ጉባኤ ምድረ ቀደምት ሀገር ወደሆነችው ኢትዮጵያ የሚመጡ ተሳታፊዎችን ለመቀበል ዝግጁ ነን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN ኅዳር 2/2019 ዓ.ም

ከመላዉ ዓለም ለCOP32 ጉባኤ ምድረ ቀደምት ሀገር ወደሆነችው ኢትዮጵያ የሚመጡ ተሳታፊዎችን ለመቀበል ዝግጁ ነን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ ይገኛል። ጉባዔዉ “ጉዞ ወደ ዘላቂ፣ አይበገሬነት እና ፍትሃዊነት ወደተረጋገጠበት መጻኢ ዘመን” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ነዉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የአየር ንብረት እርምጃን ከኢኮኖሚ ፖሊሲዋ ጋር አስተሳስራ እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።

‎እርምጃዉ የዜጎችን የእለት ተእለት ኑሮ ለማሻሻል፣ የመቋቋም አቅምን ለማጠናከር እና የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን ዘላቂ ለማድረግ እጅግ ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በመደመር ፍልስፍናችን እየተመራን፣ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብራችን እስካሁን ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ችለናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የታዳሽ ኃይል ልማትን፣ ዘላቂ የከተማ ግንባታን እና የአየር ንብረት ተስማሚ መፍትሄዎችን በስፋት እያሳደግን እንገኛለን ብለዋል፡፡

‎አሁን ላይ ከቃል ኪዳን ባለፈ ወደ ፈጣን ተግባራዊ እርምጃዎች መሸጋገር ይኖርብናል ነዉ ያሉት፡፡ ይህም በቀላሉ ሊገኝ በሚችል የአየር ንብረት ፋይናንስ፣ ይበልጥ ጠንካራ በሆኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች እና ተጋላጭ ለሆኑ ማህበረሰቦች የመቋቋም አቅም ግንባታ ላይ በሚደረግ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ተግባራዊ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡

‎ኢትዮጵያ መጪውን የCOP32 ፕሬዝዳንትነት ስትረከብ እነዚህን ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በግንባር ቀደምትነት የምታራምድ መሆኑን በመግለጽ ስኬታማ ውጤት እንዲመዘገብም ከCOP31 ፕሬዝዳንት ጋር በቅርበትና በትብብር ትሠራለች ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ከመላው ዓለም ለCOP32 ጉባኤ ምድረ ቀደምት ሀገር ወደሆነችው ኢትዮጵያ የሚመጡ ተሳታፊዎችን ለመቀበል ዝግጁ ነን ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2027 የሚካሄደውን የኮፕ 32 የአየር ንብረት ጉባኤ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ታካሂዳለች፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review