AMN- ኅዳር 2/2019 ዓ.ም
የአፍሪካን ባህል፣ ኪነ-ጥበብ፣ ፈጠራ እና ሥራ ፈጣሪነትን የሚያስተዋውቀው “የአፍሪካ ሴሌብሬትስ 2026” ፌስቲቫል በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ በይፋ ተከፈተ።
ፌስቲቫሉ “አንዲት አፍሪካ፣ አንድ ህዝብ፡ ባህልን፣ ፈጠራን እና ስራ ፈጣሪነትን ለጋራ የበለፀገ የወደፊት ጊዜ ማስተሳሰር” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ሲሆን፤ የአፍሪካን ባህላዊ፣ የተፈጥሮና የሰው ኃይል እምቅ አቅም ወደ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመቀየር ያለመ ነው።
በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የባህልና የሃይማኖት መሪዎች፣ አርቲስቶች፣ ሥራ ፈጣሪዎች፣ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች እና የተለያዩ ዘርፍ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
ከህዳር 2 እስከ 6/2019 ዓ.ም በሚቆየው በዚህ ፌስቲቫል ላይ ከ45 የአፍሪካ ሀገራት እና ከ17 የሌሎች ዓለም ሀገራት የተውጣጡ ተሳታፊዎች ታድመዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀፍታይ ገብረእግዚአብሔር በመክፈቻው ላይ እንደተናገሩት፤ አዲስ አበባ የነፃነት አርማ የሆነው የአድዋ ድል የተመዘገበባት፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሠረተባት እና ታላላቅ የዲፕሎማሲ ማኅበረሰቦች መገኛ መሆኗን አስታውሰዋል።
ኃላፊው አክለውም የአድዋ ላይ አፍሪካ ልትሸነፍ እንደማትችል የተረጋገጠበት ነበር፤ ዛሬ ደግሞ የእኛ ኃላፊነት አፍሪካ ልትከፋፈል እንደማትችል ማረጋገጥ ነው ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።
‘አፍሪካ ሴሌብሬትስ’ ታሪክን ብቻ ከማውሳት ባለፈ በኪነ-ጥበብ፣ በባህል፣ በቅርስ፣ በቴክኖሎጂ እና በንግድ ዘርፎች ወጣት ፈጣሪዎችን ከፖሊሲ አውጪዎች እንዲሁም አርቲስቶችን ከባለሀብቶች ጋር የሚያገናኝ የጋራ ብልጽግና መድረክ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

አቶ ሀፍታይ ከተማዋ እያካሄደች ያለውን የኮሪደር ልማት፣ አዳዲስ የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎች እና የዘመናዊ እንግዳ ተቀባይነት ዘርፍ ማሻሻያዎችን በማንሳት፤ የፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች ከተማዋን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።
እስከ ህዳር 6 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ በሚቆየው በዚህ ፌስቲቫል፤ በቀጣይ ቀናት በአፍሪካ ባህል፣ ኪነ-ጥበብ፣ ቅርስ፣ ፈጠራ ኢንዱስትሪዎች እና ሥራ ፈጣሪነት ዙሪያ የተለያዩ የውይይት መድረኮች እንደሚካሄዱ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መረጃ ያመለክታል።