AMN- ነሐሴ 14/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን በሦስት ዓመት ውስጥ 45 ሚሊየን ብር የሚያስገኝለት ስምምነት ተፈራርሟል።
በጁፒተር ሆቴል በተከናወነው ስነ ስርዓት ላይ ፌዴሬሽኑ ከቫርዳስ ኢንተርቴመንት እና ኒዮ ማርኬቲንግ ጋር በጋራ ለመስራት ተስማምቷል።
ስምምነቱ በዋናነት ዘንድሮ በሚከናወነው 20ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጀምሮ ለሦስት ዓመት ይቆያል።
ቫርዳስ ኢንተርቴመንት እና ኒዮ ማርኬቲንግ ለሦስት ዓመት የሚቆይ የንግድ መብት ሽያጩን ይወስዳሉ። የሚዲያ መብት ፣ ስፖንሰሮች ሌሎች ጉዳዮችንም ይቆጣጠራሉ።
ከፌዴሬሽኑ ጋር በጋራ ለመስራት የተስማሙት ሁለቱ ድርጅቶች ከጨዋታ በፊት ፣ ከጨዋታ መሀል አዝናኝ ዝግጅቶች ያሰናዳሉ። በዋናነት በጨዋታ እረፍት ሰዓት ታዋቂ ሙዚቀኞች ስራቸውን እንዲያቀርቡ ይደረጋል ተብሏል።
ከዚህ ውጪ ደጋፊዎችን ወደ ስታዲየም ሊስቡ የሚችሉ እና የአዲስ አበባን ገፅታ ሊያሳዩ የሚችሉ ሌሎች ዝግጅቶች እንደሚኖሩ በተሰጠው መግለጫ ላይ ተነስቷል።
የስታዲየም ትኬት ሽያጭ ግን ሙሉ ለሙሉ ገቢው የፌዴሬሽኑ እንደሆነ ተገልጿል።
ስምምነቱን በፌዴሬሽኑ በኩል ም/ፕሬዝዳንቷ ማስተዋል ወንደሰን ፣ በቫርዳስ በኩል አቶ ተስፉ ስንታየሁ እንዲሁ ከኒዮ ማርኬቲንግ ፊሊሞን መንገሻ ተወክለው ውል ተፈራርመዋል።
በተያያዘ 20ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የሚካሄድበት ቀን እና ተሳታፊ ክለቦች ታውቀዋል። ከመስከረም 9-26 በአዲስ አበባ ስታዲየም በሚከናወነው ውድድር ላይ ስምንት ክለቦች ይሳተፋሉ።
ከአዲስ አበባ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ መቻል ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም ኢትዮጵያ መድን ይሳተፋሉ። ጋሞ ጨንቻ እና አዳማ ከተማ በተጋባዥነት ይወዳደራሉ።
በሸዋንግዛው ግርማ