AMN – ኅዳር 13/2019 ዓ.ም
በአትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ እና ባልደረቦቹ አነሳሽነት የተጀመረው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከስፖርታዊ ውድድርነቱ አልፎ የሃገርን ገጽታ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡
ዉድድሩ የሃገር ውስጥ እና የውጭ ሃገራት ታዋቂ አትሌቶችና ጋዜጠኞችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች የሚሳተፉበት መሆኑ ደግሞ ልዩ ያደርገዋል፡፡
የጎዳና ላይ ሩጫው በርካታ የሃገር ውስጥ ተሳታፊዎች የሚታደሙበት በመሆኑ የህዝቦችን አንድነት፤ ወንድማማችነትና አብሮነት በማጠናከር ረገድ ያለው ሚናም የላቀ ነው፡፡
አዲስ አበባ በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት አዲስ ገጽታን ተላብሳ፤ ደምቃና ተውባ ውድድሩን ማስተናገድ መጀመሯም ለዉድድሩ አዲስ ድባብና ውበት ጨምሯል፡፡
ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኢትዮጵያን የስፖርትና የቱሪዝም እድገት ይበልጥ እንዲነቃቃ ትልቅ ዐቅም ሆኗል፡፡
ውድድሩ በዓለም አትሌቲክስ ዕውቅና የተሰጠው ሲሆን፣ የአፍሪካ ትልቁ የጎዳና ላይ ሩጫ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ዘንድሮ የሚካሄደው ዉድድርም፤ ታላቁ ሩጫ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቁ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር እንዲሆን ለተጀመረው ጥረት ተጨማሪ ዐቅም ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል፡፡
ኢትዮጵያ የታላላቅ አትሌቶች መፍለቂያ እንደመሆኗ መጠን ውድድሩ የበርካቶችን ቀልብ እየሳበ፤ የተሳታፊዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ይገኛል፡፡
ዉድድሩ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ጭምር ለተቀረው ዓለም የሚሰራጭ በመሆኑ የኢትዮጵያን ባህል፣ ሙዚቃና መስተንግዶ ለተቀረው ዓለም ያስተዋውቃል፡፡

ዛሬ የሚካሄደዉ 26ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ከ60 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ይሮጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ውድድሩ የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ልዕልና፣ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል እና የመዲናዋ ዘመናዊ ገጽታ ለተቀረው ዓለም አቀፍ የሚተዋወቅበት ታላቅ መድረክ ነው፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከዋናው የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር በተጨማሪ የሴቶች ብቻ ሩጫ፣ የህጻናት ሩጫ እና በክልል ከተሞች የሚደረጉ የግማሽ ማራቶን ውድድሮችንም ያዘጋጃል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከስፖርታዊ ፉክክር ባለፈ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በሙዚቃ፣ በጭፈራና በአንድነት መንፈስ የሚደምቁበት ታላቅ ህዝባዊ በዓል ነው።
በወንድማገኝ አሰፋ