አዲስ አበባ የስፖርት ልህቀት መናኸሪያ እየሆነች ነው

You are currently viewing አዲስ አበባ የስፖርት ልህቀት መናኸሪያ እየሆነች ነው

AMN- ኅዳር 13/2019 ዓ.ም

የመደመር መንግሥት ሰው ተኮር የልማት እሳቤን መሠረት በማድረግ ለስፖርቱ ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት፣ በአዲስ አበባ ከተማ የስፖርት መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት፣ ተተኪ ስፖርተኞችን በማፍራት እና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በማስተናገድ ረገድ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በመዲናዋ የተከናወኑት የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች ከመንገድና ውበት ስራዎች ባለፈ ለነዋሪዎች ምቹ የሆኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን አካተው ተገንብተዋል፡፡

በሁሉም ክፍለ ከተሞች ለእግር ኳስ፣ ለቅርጫት ኳስ፣ ለመረብ ኳስ፣ ለሳይክል እና ለስኬት ስፖርቶች የሚያገለግሉ በርካታ የማዘውተሪያ ሜዳዎች ተገንብተው ለወጣቱ ትውልድ በነፃ ክፍት እንዲሆኑ ተደርጓል።

ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የሚያሟላውና ከ60 ሺህ በላይ ተመልካቾችን በወንበር የመያዝ አቅም ያለው የግዙፉ አደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ መፋጠን እንዲሁም የአዲስ አበባ እና የአበበ ቢቂላ ስታዲየሞች አጠቃላይ የደረጃ ማሻሻያ እድሳት መከናወኑ ከተማዋን ለታላላቅ ውድድሮች ብቁ እያደረጋት ይገኛል።

የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መስፋፋት የመዲናዋን ወጣቶች አካላዊና አእምሯዊ ብቃት ከመገንባት ባለፈ፣ ለሀገር ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ሰፊ ዕድል ፈጥሯል፡፡

በአዲስ አበባ በተቋቋሙ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላትና ማዘውተሪያ ስፍራዎች የሰለጠኑ ታዳጊዎች ወደ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች እና ብሔራዊ ቡድኖች እየተቀላቀሉ ይገኛሉ።

በየአካባቢው የተዘጋጁት የእግረኛ፣ የሩጫ እና የብስክሌት መንገዶች ነዋሪዎች በየዕለቱ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን እንዲያዘወትሩ በማድረግ ጤናማ ማህበረሰብ የመፍጠር ሂደቱን አጠናክረዋል።

አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ መዲና ከመሆኗ ጎን ለጎን፣ የአህጉርና ዓለም አቀፍ የስፖርት ሁነቶች ማዕከል እንድትሆን እየተሰራ ነው፡፡

ከተማዋ የተለያዩ አህጉር አቀፍ የአትሌቲክስ፣ የእግር ኳስ እና የሌሎች ስፖርቶች ውድድሮችን እንዲሁም የስፖርት ቱሪዝም ፌስቲቫሎችን ለምሳሌ ታላቁ ሩጫ፣ የሳይክል ፌስቲቫሎች እና ዓለም አቀፍ የቦክስ ውድድሮች በብቃት በማስተናገድ የሀገሪቱን በጎ ገጽታ እየገነባች ትገኛለች።

በመዲናዋ ማሰልጠኛ ማዕከላት የተገነቡ ስፖርተኞች፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች እንደ ዳካር 2026 የወጣቶች ኦሊምፒክ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሻምፒዮናዎች ኢትዮጵያን ወክለው አኩሪ ድሎችን ማስመዝገብ ችለዋል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review