መንግስት ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ህብረተሰቡ ላይ ጫና የሚፈጥሩ የትኛዉንም አይነት ድርጊቶች እየተከታታለ እርምጀ ይወስዳል- ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)

You are currently viewing መንግስት ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ህብረተሰቡ ላይ ጫና የሚፈጥሩ የትኛዉንም አይነት ድርጊቶች እየተከታታለ እርምጀ ይወስዳል- ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)

AMN – ጥር 1/2017 ዓ.ም

መንግስት ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ህብረተሰቡ ላይ ጫና የሚፈጥሩ የትኛዉንም አይነት ድርጊቶች እየተከታታለ እርምጀ እንደሚወስድ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) አመላከቱ፡፡

እንደ ዓለም አቀፉ የፔትሮል ዋጋ መረጃ፣ የጥር ወር የመጀመሪያዎቹ ቀናት የዓለም አቀፉ የነዳጅ መሸጫ አማካይ ዋጋ በሊትር 1.25 የአሜሪካን ዶላር መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በኢትዮጵያ በሊትር በ0.805 የአሜሪካን ዶላር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ዋጋ ከዓለም አቀፉ አማካይ የመሽጫ ዋጋ የ35 በመቶ ቅናሽ ያለው መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

ከምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች አኳያም ካየነው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በእጅጉ ያነሰ እንደሆነ ግልጸዋል፡፡

ለምሳሌ በኬንያ 1.351፣ በሩዋንዳ 1.136፣ በኡጋንዳ 1.299፣ በታንዛንያ 1.127 የአሜሪካን ዶላር በሊትር በተመሳሳይ ወቅት እየተሸጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

እጅግ ደሃ በሚባሉት እንደ ማላዊ በ1.459፣ ማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብልክ 1.746 የአሜሪካን ዶላር በሊትር እየተሸጠ እንደሚገኝም ነው ያነሱት፡፡

በአብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ከ1.3 የአሜሪካን ዶላር በላይ እየተሸጠ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ እውነታው ይህ ሆኖ እያለ የሰሞኑን የነዳጅ ጭማሪ ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰላም መሆን የእግር እሳት የሚሆንባቸው አንዳንድ ወገኖች እንደተለመደው በባንዳነት ተግባራቸው ተጠምደዋል ብለዋል።

እነሱ የሚኖሩባቸው ሀገሮች የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ፈጽሞ አይታያቸውም ያሉት ሚኒስትሩ፣ ራሳቸውን ለህዝቡ አሳቢና ተቆርቋሪ ሌላውን ደግሞ ለህዝቡ ችግሮች ደንታ ቢስ አድርገው ያቀርባሉ ሲሉም አክለዋል።

ይህን የሚያደርጉት እዉነታዉን ስለማያዉቁ ሳይሆን ድብቁ ባህሪያቸው እንደይገለጥ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ተሳስተዉ እንኳን በየአካባቢዎቹ ስላለዉ በጎ የልማት እንቅስቃሴ፣ የሰላም ሁኔታ፣ በህብረተሰብ መካካል መግባባት የሚፈጥሩ ጉዳዮችን እንደማያነሱም ነው ያመላከቱት፡፡

ለምን ቢባል ይህ ሃሳቦችን ማመንጨት፣ ጥናትና ፈጠራ፣ ተጨባጭ አብነትና የሀሳብ ልዕልናን እንደሚጠይቅ ነው ያነሱት፡፡

እነሱ ይህ የላቸዉም ያሉት ሚኒስትሩ፣ በየአካባቢው የተፈጠሩ ትናንሽ ክስተቶች በወሬ ለቃሚዎቻቻዉ አማካይነት እየቃረሙ ቆርጦ በመቀጠል እኩይ ፍላጎታቸዉን ለማሳካት እንደሚያውሉት ጠቁመዋል፡፡

የሚያተርፉት ከግጭት፣ ከሁከትና ግርግር የሆነው እነዚህ አካላት፣ ሰው መረጃ የሚያገኝ የማይመስላቸው፣ ነውር የሚባል ነገር በደጃቸው ያልዞረ፣ ነፃ ገበያ እና በነፃ ገበያው ውስጥ የመንግስት ሚና ሚዛን መጠበቅ መሆኑ ለነሱ ምንም የሆነባቸው መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በነጻ ገበያ ዉስጥ ይቅርና በሶሻሊስት ስርዓት መንግስት እንዲያደርግ የማይገደድባቸዉ ጉደዮችን በማንሳት መንግስትን ይከሰሉ ያሉዋቸው እነዚህ አካላት፣ መረጃዎችን በማዛባት ለራስ እኩይ የፖለቲካ ፍላጎት ለመጠቀም የሚደረግ ሙከራ የቱንም ያህል ርቀት አይወስድም ሲሉ አስገንዝበዋል።

መንግስት ልማትን ለማፋጠን የሚወሰዱ እርምጃዎች በማህበረሰቡ ላይ ጫና ሊያሳድሩ እንደሚችሉ እንደሚገነዘብ የገለጹት ዶክተር ለገሰ፣ በጥንቃቄ መፈፀም እንደሚገባም ያለውን እምነት ገልጸዋል።

ለዚህም አቅዶ እና አልሞ የህብረተሰቡን ዘላቂ ጥቅም መሠረት አድርጎ እንደሚሠራ በማንሳት፣ ሸክሙንም በመጋራት ጊዜያዊ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ያለውን መረዳት አስገንዝበዋል።

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ መንግስት ለነዳጅ፣ ለአፈር ማዳበሪያ፣ ለመድሃኒት እና መሰል የጤና ጉዳዮች ወዘተ ከፍተኛ የሚባለውን ድጎማ እያደረገ መሆኑን ያመላከቱት ሚኒስትሩ፣ ለዚህም በዓመት ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

መንግስት መደበኛ ተግበራትንም እያከናወነ መሆኑን በመግለፅ፣ ከዚህ ባልተናነሰ መልኩ ፍጥነት እና ፈጠራን መሠረት ያደረጉ ለነገው ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑና የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን የሚያደርጉ ሀገራዊ ኢንሼቲቮች እና የልማት ፕሮግራሞችን እውን እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም የሰብል ምርት (የስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽለ፣ገብስ፣ሩዝ፣ ጤፍ)፣ የሌማት ቱሩፋት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ኢንሼቲቮች ወደ ሁሉም አካባቢዎች ወርደው በውጤታማነት እየተተገበሩ ነው ብለዋል።

የኮሪደር ልማቱም የኢትዮጵያን ህዝብ የሚመጥኑ ከተሞችን እየገነባ ነው ያሉት ዶክተር ለገሰ፣ የገጠሩን የአኗኗር ሁኔታና የመሠረተ ልማት አቅርቦት ታሳቢ ያደረገ ስራም ተጀምሯል ብለዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በማዕድን ዘርፍ በተለይም በወርቅ ማዕድን ላይ የተደረገው ማሻሻያ ገና ግማሽ ዓመት ሳይሞላ ለሀገሪቷ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እያስገኘ መሆኑንም አመላክተዋል።

ህዝቡንም ተጠቃሚ በማድረግ የአኗኗር ዘይቤውን እየለወጡት መሆኑን በቅርቡ በሚንስትሮች ደረጃ በሁሉም ክልሎች የተደረገው ድጋፋዊ ሱፐርቪዥን አረጋግጧል ብለዋል።

መንግስት ሰላምን በማስፈን የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ውጤታማ እየሆነ እንዳለ በማንሳትም እነዚህን ማጽናት፣ ዘላቂ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

አጋጠሚዉን በመጠቀም ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ህብረተሰቡ ላይ ጫና የሚፈጥሩ የትኛዉንም አይነት ድርጊቶች እየተከታታለ እርምጀ እንደሚወስድም አመላክተዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review