AMN- ነሐሴ 9/2018 ዓ.ም.

በ2018 በጀት ዓመት ከህዝቡና ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በተደረገ ቅንጅት፣ ከባድ ወንጀሎችን በ53 በመቶ፣ ቀላል ወንጀሎችን ደግሞ በ43 በመቶ መቀነስ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ ተናገሩ።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ እና የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ምዘና የዕውቅናና የሽልማት መድረክ እያካሄደ ይገኛል።

ባለፈው የበጀት ዓመት የተቀመጡ ዕቅዶችን ከግብ ለማድረስ በተከናወኑ የተቀናጁ ሥራዎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውንም የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ገልጸዋል።

ለተመዘገበው ስኬት የህዝብ ተሳትፎና የፀጥታ ቅንጅት፣ የአቅም ግንባታና የሪፎርም ሥራዎች፣ የቅድመ መከላከልና የመረጃ ሥራ እንዲሁም የጎረቤት ከተሞች ትብብር ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል፡፡

ቢሮው በአዲሱ የበጀት ዓመት በተቋም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ ትግበራ እና በህብረተሰብ ተሳትፎ ላይ አተኩሮ እንደሚሠራ የገለጹት ወይዘሮ ሊዲያ፣ በከተማዋ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መጠን በ2018 ከነበረበት አፈጻጸም ተጨማሪ በ20 በመቶ ለመቀነስ የሚያስችል ዝርዝር ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መግባቱን አብራርተዋል።

በቀጣዩ የበጀት ዓመት ለአገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋነት፣ ለህዝብ ፍላጎት ምላሽ እና ለሰላም እሴት ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ የተገለጸ ሲሆን፣ ከፌደራል እና ከሸገር ከተማ የፀጥታ መዋቅሮች ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሠራር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመላክቷል።
በቴዎድሮስ ይሳ