AMN- ነሐሴ 9/2018 ዓ.ም

ከ22 ጎላጉል እስከ ኤድናሞል አደባባይ ያለው መስመር በሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት በከፍተኛ ፍጥነት እየተገነቡ ካሉ ዋና ዋና አካባቢዎች አንዱ ነው።

ልማቱ ሰፋፊ የተሽከርካሪ፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችን ጨምሮ የታክሲ መጫኛና ማውረጃ፣ የተሽከርካሪዎች ማቆሚያ እንዲሁም የአረንጓዴ ስፍራዎችን አካቷል።


አካባቢው ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የትራፊክ መጭናነቅ የሚታይበትና ለእግረኛም ሆነ ለአካባቢው ነጋዴዎችና የሕንፃ ባለቤቶች ምቹ እንዳልነበረ ይገለጻል።
ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉ የአካባቢው ነዋሪዎች እና የሕንፃ ባለቤቶች እንደገለጹት፣ ልማቱ የአካባቢውን የንግድ እንቅስቃሴና ገጽታ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል።

በ22 አካባቢ የንግድ ህንፃ ባለቤት አቶ ዳንኤል ቲመርጋ፣ አካባቢው በንግድ ማዕከልነት የሚታወቅና ከመርካቶ ቀጥሎ ሊጠራ የሚችል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የነበረው የንግድ እንቅስቃሴውም ሆነ ሱቆቹ እና አካባቢው የነበራቸው ገጽታም የሚመጥን እንዳልነበረ ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት እግረኞችም በተሸከርካሪ መንገድ ይሄዱ እንደነበር በማስታወስ፣ አሁን ግን ሰፊ የተሸከርካሪ፣ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶች መገንባታቸው ለአካባቢው የተሸለ ነገር ይዞ ይመጣል ብለዋል፡፡
ሌላኛዋ የ22 አካባቢ የንግድ ህንፃ ባለቤት ወ/ሮ ትዕግስት ተስፋዬ፣ አሁን ላይ አካባቢው ከፍተኛ ለውጥ እንዳለው ይናገራሉ።
ከኮሪደሩ በፊት የነበረው የተበላሸ የአካባቢው ገፅታ፣ ኮሪደር ሲመጣ በመለወጡ እንኳን ለሌላ ሰው እኛም ተሳስተን አልፈን እስክንሄድ አድርሶናል ብለዋል።

በአካባቢው ማማር እና መለወጥ ንግዱም እየሰፋ እንዲሄድና ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆን ያደርጋል ሲሉም አክለዋል፡፡
የ22 ፓርኪንግ ፕላዛ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር መለሰ ሳህሌ በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ ከመሬት ሥር ሁለት ወለል እና ፕላዛ ያለው ሲሆን፣ 165 መኪና ማስቆም የሚችል መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን አፈጻጸሙ 80 በመቶ መድረሱን በመግለፅም፣ ቀሪ የኤሌክትሮ መካኒካል፣ የፊኒሺንግ እና የኤሌክትሪካል ሥራ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማቱ በተያዘለት ጊዜና ጥራት እንዲከናወን ከማዕከል ጀምሮ የወረዳ እና የክፍለ ከተማ ባለሙያና አመራሮች ክትትል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረውም ተመላክቷል።
በታምራት ቢሻው
See less