የባለሀብቱን ገዳይ እና አስገዳይን ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ

You are currently viewing የባለሀብቱን ገዳይ እና አስገዳይን ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ

AMN ጥር 12/2017 ዓ.ም

አቶ ቢረሳው ምናለ ፈንታ የተባሉት ግለሰብ ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ለሚ ኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 9 ልዩ ቦታው አትሌቶች መንደር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡

ታህሳስ 21 ቀን 2017 ዓ/ም ከምሽቱ 2:00 ሰዓት ከስራ መልስ ወደ ቤታቸው በማምራት በራቸው ላይ ቆመው የመኪና ጥሩምባ እያሰሙ በር እስኪከፈትላቸው እየጠበቁ በነበረበት ወቅት ማንነቱ ባልታወቀ ግለሰብ በተተኮሰባቸው ሦስት ጥይት ህይወታቸው አልፏል፡፡

ፖሊስ የወንጀሉ መፈፀም ሪፖርት ከደረሰው ሰዓት ጀምሮ በወንጀሉ ስፍራ ፈጥኖ በመድረስ የወንጀል ፈፃሚውን ማንነት ለማወቅና በቁጥጥር ስር ለማዋል ቀን ከሌት ያልተቋረጠ እና እልህ አስጨራሽ ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ከወንጀሉ ጀርባ ያሉ ግለሰቦችን ማንነትና ምንነት ለመለየትም ከአዲስ አበባ ሐዋሳ እስከ ሞያሌ ጫፍ የደረሰ መረጃና ማስረጃዎችን የማሰባሰብ ተግባር ተከናውኗል።

በፖሊሳዊ ጥበብ እና ስልት በተሰራው በዚህ ስራ ወንጀሉን በመፈፀም የተጠረጠረውን መኮንን ይዋል ይፍሩ የተባለውን ግለሰብ እና አብዩ አይተነው ፈንታ ጨምሮ ለወንጀሉ መፈፀም አካባቢውን በመቆጣጠር ተሳትፎ የነበረውን አቶ ወርቁ መለሰ ካሴ የተባሉትን ሦስቱንም ተጠርጣሪዎች በደቡብ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጌዴዎን ዞን ይርጋ ጨፌ ከተማ ላይ በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ከወንጀሉ መፈፀም በፊት በተቀነባባረ ሴራ በቂ ዝግጅት ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን የግድያ ወንጀሉን የፈፀመው መኮንን ይዋል ይፍሩ የተባለው ግለሰብ በህገ-ወጥ መንገድ በታጠቀው ማካሮቭ ሽጉጥ የአቶ አብዩ አይተነው ፈንታ የግል ጠባቂ ሆኖ ሲያገለግል እንደቆየ ተጠቁሟል።

ሁለቱ ግለሰቦች ከአቶ አብዩ አይተነው ፈንታ በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሰረት አንዱ የአካባቢውን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ለወንጀል ፈፃሚው ሁኔታውን ሲያመቻች መኮንን ይዋል ይፍሩ የተባለው ደግሞ የግድያ ወንጀሉን መፈፀሙን ለፖሊስና ለፍርድ ቤት ከሰጡት የእምነት ቃል የተረጋገጠ ከመሆኑም ባሻገር በወንጀሉ ስፍራ የመርማሪዎችንና አቃቤ ህግ ቡድን እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት የወንጀሉን አፈፃፀም መልሶ ማቋቋም (Re-construct) በተግባር አሳይተዋል፡፡

በዕለቱም የወንጀሉ ፍሬ የሆነው ንብረትነቱ የአቶ አብዪ አይተነው ፈንታ የውግ ቁጥር የሌለው ማካሮቭ ሽጉጥ እና ለማምለጥ የሞከሩበት እንዲሁም ሽጉጡን የደበቁበት ላንድክሩዘር ተሽከርካሪ በኤግዚቢትነት ተይዟል ፡፡

ምንም እንኳን ተጠርጣሪዎቹ ማንነታቸውን በመቀየር ከወንጀሉ ተጠያቂነት ለማምለጥ በሐሰተኛ ስም ሐሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት ከኢትዮጵያ በሞያሌ በኩል ወደ ኬንያ ለመጥፋት ቢያስቡም በተሰራው እረፍት አልባ ፖሊሳዊ ጥበብ በታከለበት የክትትልና የምርመራ ስራ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በቅንጅት ሰርተዋል፡፡ የሲዳማ ክልላዊ መንግስት ፖሊስ ኮሚሽን በዚህ የክትትል ስራ ውስጥ የጎላ ተሳትፎ እና ትብብር ማድረጉም ተጠቅሷል፡፡

የተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋል ወንጀል ፈፅሞ ከህግ ተጠያቂነት ማምለጥ እንደማይቻል የሚያረጋግጥ ተግባር መሆኑን የጠቀሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ፤ የህብረተሰቡን አቅም በመጠቀም ውጤት መገኘቱን አመላክቷል፡፡

በቀጣይም በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሚደረጉ የፍትህ ሂደቶች ውሳኔውን ተከታትሎ ለህዝብ እንደሚያቀርብ የአዲስ አበባ ፖሊስ በመረጃው ገልጿል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review