AMN – መጋቢት 12/2017
የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ለአምስት አዳዲስ ድርጅቶች የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ መስጠቱን አስታወቀ፡፡
ባለስልጣኑ ለካፒታል ገበያው እንቅስቃሴ ቁልፍ ሚና ለሚኖራቸው የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ የመስጠት ሥነ-ሥርዓት በአዲስ አበባ አካሂዷል።
በሥነ-ስርዓቱ ላይ የብሔራዊ ባንክ ገዥ እና የካፒታል ገበያ ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢ ማሞ ምህረቱ፥ ባለስልጣኑ ለአምስት የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ መስጠቱን አስታውቀዋል።
ይህም ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት መሻሻል ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አስገንዝበዋል።
የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልቁ፥ ገበያው ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ሚና ቢኖረውም በአግባቡ ሳይሰራበት ቆይቷል ብለዋል።
ይህንኑ ተከትሎ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን በማቋቋምና የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹ የኢንቨስትመንት ባንኮችንና የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ አከናዋኝ ፍቃድ የተሰጠበት እና አጠቃላይ ፍቃድ የተሰጣቸው የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎችን ቁጥር ከአራት ወደ ዘጠኝ ከፍ ያደረገ ነው::
በዛሬው ዕለት አምስት የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ ወስደዋል፡፡
ለሲቢኢ ካፒታል አ.ማ ኢንቨስትመንት ባንክ፣ ለወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ አ.ማ፣ ለኢትዮ-ፊደሊቲ ሴኩሪቲስ አ.ማ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ አከናዋኝ፣ ለኤች ኤስ ቲ ኢንቨስትመንት አድቫይዘሪ ሰርቪስስ ኃ.የተ.የግ.ማ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪ እና ለኢኩዥን የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪ ኃ.የተ.የግ.ማ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪ ፈቃድ ተሰጥቷል ብለዋል።
አዲሶቹ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ስኬትና ዘላቂነት በማረጋገጥ ገበያውን ለመቅረጽ የሚጫወቱት ሚና ወሳኝ መሆኑን ማስገንዘባቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡