ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገሩ ናቸው- ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

You are currently viewing ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገሩ ናቸው- ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

AMN-መጋቢት 22/2017 ዓ.ም

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገሩ መሆናቸውን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለፁ።

በግብርና ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን እና የአደጋ መከላከል አቅምን በሚመለከት የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን(ዶ/ር) እንዲሁም የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) አብራርተዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በግብርናው ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግርን ማምጣት የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) አንስተዋል።

በተለይ የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴንና የሜካናይዜሽን እርሻን የማስፋት እንዲሁም በዝናብ ላይ ጥገኛ የነበረውን ግብርና በመቀየር ዓመቱን ሙሉ ወደ ማረስ መገባቱን ጠቅሰዋል።

ይህም ምርትና ምርማነትን በማሳደግ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሻገረ መሆኑን ገልፀዋል።

በሌላ በኩል በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለውን ስኬት ዘላቂ ለማድረግ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ- ግብር አማካኝነት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ልማት ለመተግበር እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የአስር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን ነው የተናገሩት።

በዚህም ከለውጡ በፊት በመኸር 12.5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ይታረስ እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁን ላይ ወደ 20.5 ሚለየን ሄክታር ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰበሰበውን ምርት ከ293 ሚሊየን ኩንታል ወደ 608 ሚሊየን ኩንታል ምርት ከፍ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።

አያይዘው ከለውጡ ወዲህ ባሉት ዓመታት የስንዴ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ኢትዮጵያ ራሷን እንድትችል በተጀመረው ኢኒሼቲቭ ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።

በመኸር ብቻ የሚገኘው ዓመታዊ የስንዴ ምርት ከ48.5 ሚሊየን ኩንታል ወደ 152 ሚሊየን ኩንታል ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።

በ2011 ዓ.ም በ3 ሺህ 500 ሄክታር መሬት የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ደግሞ፣ አሁን ወደ 3.5 ሚሊየን ሄክታር ማደጉን በማንሳት ከዚህም 172 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በግብርናው ዘርፍ እየተገኘ ያለው ስኬት የአደጋ ስጋትን በራስ አቅም ለመቋቋም የተጀመረውን ስራ እያገዘ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ናቸው።

ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመቻል ፖሊሲ ተቀርፆ በሁሉም ክልሎች ወደ ስራ መገባቱን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review