በጤና ዘርፉ ላይ ሁከት በመፍጠር እና የታካሚዎችን ህይወት አደጋ ላይ በመጣል የተጠረጠሩ 47 የጤና ባለሙያዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ ማጣራት መጀመሩን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ

AMN-ግንቦት 15/2017 ዓ.ም

ሰሞኑን የጤና ባለሙያዎች ያነሱትን የመብት ጥያቄ ሽፋን በማድረግ በሀገሪቱ ትርምስ እንዲፈጠር ከሚሠሩ ኃይሎች ጋር በማበር ሕገ ወጥ የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ፣ በጤና ዘርፉ ላይ ሁከት በመፍጠር እና የታካሚዎችን ህይወት አደጋ ላይ በመጣል የተጠረጠሩ 47 የጤና ባለሙያዎችን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ ማጣራት መጀመሩን አስታውቋል፡፡

እነዚህ ተጠርጣሪዎች የጤና ባለሙያዎች ያነሱትን የደመወዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ እንደሽፋን በመጠቀም ሕገ-ወጥ የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ፤ ሌሎችም ሥራ እንዲያቆሙ ለአድማ በማነሳሰት፣ የታካሚዎች ሕይወት ለሞትና ለአደጋ እንዲጋለጥ በማድረግ ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር የተጠረጠሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በተለያዩ የጤና ተቋማት የአድማ መረቦችን በመዘርጋት፤ የጤና ባለሙያ ያልሆኑ አካለትን ነጭ ጋዋን በማስለበስ የሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ ገብተዉ ሁከት እንዲፈጥሩ በማድረግ፣ ያልተገባ ወሬ በመንዛት እና በተለያየ መንገድ ሰላማዊ የሕክምና ሂደትን በማደናቀፍ የሕሙማንና የጤና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ እንዲወድቅ በማድረግ፣ በመንግሥት የሕክምና አገልግሎት እና ትምህርት በሚሰጥባቸው ተቋማት ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲስተጓጎል ማድረጋቸው ተመላክቷል፡፡

እንዲሁም ሙያቸውን አክብረው በሥራ ላይ በተገኙ ባልደረቦቻቸው ላይ ዛቻ እና ማስፈራራት ከማድረስ ባለፈ ሁከት እንዲፈጠር ሙከራዎችን አድርገዋል ያላቸውን 47 ተጠርጣሪዎች በመረጃና በማስረጃ በመለየት በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያካሄደ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የጤና ባለሙያዎቹ የሙያው ሥነ-ምግባርና ሕግ በማይፈቅደው ሁኔታ የዜጎችን ሕይወት ለሞትና ለአደጋ በማጋለጥ ሥራ ማቆም፣ ሌሎችም ሥራ እንዲያቆሙ ማነሳሳት እና ማስፈራራት፣ የወንጀል ተግባር መሆኑን በመግለጽ ሌሎችም ከዚህ ተግባር እንዲቆጠቡ አሳስቧል።

በዚህ አጋጠሚ ሕዝባቸውን እና ሕግ አክብረው አገልግሎት እየሰጡ ላሉ የጤና ባለሙያዎች ፖሊስ አስፈላጊውን ጥበቃ እንደሚያደርግ ያረጋገጠ ሲሆን ከዚህ ውጭ ሁከትና ብጥብጥን ለማስፋፋት በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ፖሊስ እየወሰደ ያለውን ሕጋዊ እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review