‹‹ለነገዋ›› የሴቶች የተሀድሶ እና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ለሚያሰለጥናቸው ሴቶች የስራ ዕድል ማመቻቸቱን መቀጠሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ቆንጅት ደበላ ገለፁ፡፡
‹‹ለነገዋ›› የሴቶች የተሀድሶ እና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል፤ የሴቶችን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ተያያዥ ችግሮችን እንዲፈታ ታስቦ ወደ ስራ የገባ ማዕከል መሆኑን ኃላፊዋ ገልፀዋል፡፡
ማዕከሉ ከዚህ ቀደም በሁለት ዙር ያሰለጠናቸውን 6 መቶ 82 ሴቶችን፤ በተለያዩ የሙያ እና ክህሎት ዘርፍ ዳብረው እንዲወጡ ያላለሰለሰ ጥረት ማድረጉን አስታውቀዋል።
ቢሮው በበኩሉ ሰልጣኞች ከማዕከሉ ከወጡ በኋላ ፤ልዩ ልዩ የስራ ስምሪቶችን ወስደው በመስራት ገቢ እንዲያገኙ ማመቻቸቱን አክለዋል፡፡
በሶስተኛ ዙር እየሰለጠኑ የሚገኙ 700 ሰልጣኞችም በመሰል የሙያ እና ክህሎት ዘርፎች ላይ ብቁ ሆነው ለሀገር እና ለወገን የሚተርፍ ስራን እንዲሰሩ መልዕክት ያስተላለፉት፤የቢሮ ኀላፊዋ የስራ ስምሪት የማመቻቸቱ ስራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም በ‹‹ለነገዋ››የሴቶች የተሀድሶ እና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ሶስተኛ ዙር ሰልጣኝ ሴቶች ዩኒፎርም የማስተዋወቅ መርሀ ግብር ተካሂዷል፡፡
በትባረክ ኢሳያስ