የአካባቢ ጥበቃ የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን የብልጽግናችን መሰረት ነው ሲሉ አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ

You are currently viewing የአካባቢ ጥበቃ የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን የብልጽግናችን መሰረት ነው ሲሉ አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ

AMN- ግንቦት 28/2017 ዓ. ም

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ፣ 2ኛውን የአካባቢ ብክለት መከላከል ሀገራዊ ንቅናቄ በይፋ አስጀምረዋል።

አቶ አደም ፋራህ በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የአካባቢ ጥበቃ የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን የብልጽግናችን መሰረት ነው ብለዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች የዜጎች ጤና እንዲጠበቅና ማህበራዊ ኑሯቸው እንዲሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ገልጸዋል፡፡

መንግስት ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር፣ በኮሪደር ልማት፣ በታዳሽ ኃይል አጠቃቀም ላይ በርካታ ስራዎች መስራቱንም ተናግረዋል።

በንቅናቄው የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የማህበረሰብን ተሳትፎ ማጎልበት፣ የህግና ሥርዓት ተገዥነትን ማስፈን እና መልካም ለሰሩ እውቅና የመስጠት ስራዎች በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የታደሙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከአረንጓዴ አሻራ፣ ወንዞች ዳርቻ ልማት፣ ታዳሽ ኃይል አጠቃቀም እና ከተማ ፅዳት አንፃር የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራትን በማስመልከት ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም በዓለም ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸው፣ በሀገራችን ይህንን ተግዳሮት ለመቀነስ እንዲያስችል በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞች መተከላቸውን አንስተዋል።

በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ የደን ሽፋን ከነበረበት የ2.8 በመቶ ወደ 20 በመቶ ማሳደግ መቻሉን አንስተው፣ በአካባቢ ጥበቃና ጽዱ ከተማ ለመፍጠር በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

በከተማዋ በጽዳት፣ በውሃ ፍሳሽ አወጋገድ፡ በብዙኃን ትርስንስፖርት እና በሌሎች ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች እንደተከናወኑ ማብራራታቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ አዲስ አበባን ጨምሮ አምስት ተቋማት ፅዱ ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ረገድ እና አረንጓዴ ኢኒሼቲቭን ለማሳካት ባከናወኑት ውጤታማ ስራዎች እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review