ስፖርት ለቱሪዝም እድገት ምን ያህል አቅም  አለው?

You are currently viewing ስፖርት ለቱሪዝም እድገት ምን ያህል አቅም  አለው?

የስፖርት ቱሪዝም በዓለም ላይ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣ የገቢ ምንጭ፣ የሀገር ገፅታ መገንቢያና የዲፕሎማሲ መሳሪያ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።  የስፖርት ፌስቲቫሎችና ውድድሮች ማለትም እንደ ማራቶን፣ እንደ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ወይም የዓለም ዋንጫ አይነት ውድድሮች እንደዚሁ የአንድን ሀገር ወይም ከተማ መሠረተ ልማት፣ ባህል እና አጠቃላይ መስህብ በማጉላት ከተማን ከዓለም ጋር በማስተዋወቅ ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡

በዓለም አትሌቲክስ ውድድር የፕላቲኒየም ደረጃ ያለው የለንደን ማራቶን፣ የዱባይ ማራቶን፣ የቫሌንሺያ ማራቶን ከጀርባቸው ያነገቡት ዓላማ ከስፖርታዊ ውድድር የሚሻግር ሲሆን በተለይም እነዚህ ከተሞች ያሏቸውን ገፀበረከቶች ለዓለም በማስተዋወቅ በዘላቂነት ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ስለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ‹The Economic Effects of a Marathon as a Sport Tourism Event› ጥናታዊ ጽሑፍ ፀሀፊው ግሪጎሪ ፓፓኒኮስ በተለይም ባለፉት አሥርት ዓመታት እንደ ማራቶን ያሉ ስፖርታዊ ፌስቲቫሎች ብዙ ጎብኝዎችን ከመሳባቸው በተጨማሪ ሀገርን ማስተዋወቂያ መሳሪያ በመሆን ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው ይላሉ፡፡

በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ መለያ ውድድር እውቅና የተሰጠው የዱባይ ማራቶን ውድድር ለዱባይ ዋና የቱሪዝም አሽከርካሪነት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለውም በምሳሌነት ይጠቅሱታል፡፡ ውድድሩ ዱባይን እንደ መሪ የቱሪስት እና የስፖርት ማዕከል በማስተዋወቅ ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትና አትሌቲክስ አፍሪካ የተሰኘው ሚዲያም ባወጣው መረጃ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ አማተር ሯጮችን ይስባል ሲል ዘግቧል።

በእንግሊዝ በካንተርበሪ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰሩ ማይክ ዊድ ስፖርት በራሱ እንደቱሪዝም መስህብነት ገቢ ከማስገኘቱም በላይ ስፖርቱን ራሱን ተጠቅሞ ደግሞ ከተሞችን በማስተዋወቅ ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ያነሳሉ፡፡ 

የማራቶን ዝግጅቶችና ውድድሮች ሰፊ ቦታና ርቀትን ስለሚፈልጉ በከተማ ልማት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለቱሪዝም እና ለብራንድ ማሻሻያ አስተዋፅዖ ያደርጋሉ። እንዲሁም የመሠረተ ልማት ማሻሻያዎችን ማበረታታት እና በነዋሪዎች መካከል የአካል ብቃት ግንዛቤን ማሳደግ ያስችላሉ። በተጨማሪም የአደባባይ ስፖርታዊ ውደድሮች ኢንቬስትመንትን ሊስቡና ለአስተናጋጅ ከተማ መልካም ገጽታ መፍጠር ያስችላል። እንደዚሁም ዓለም አቀፍ ትኩረትን ወደ ከተማው ከማምጣታቸው በተጨማሪም ማህበረሰቡ በስፖርታዊ ውድድሮች ላይ ተሳትፎውን እንዲያሳድግ ያበረታታል፣ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ያስተዋውቃል እንደዚሁም  ለአዎንታዊ የከተማ ገጽታ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ የሚያብራራው የአካል ብቃት እንቀስቃሴ አሰልጣኙ ዳንኤል ሙሉጌታ ነው፡፡

የቱሪስት መስህቦችን ለማስተዋወቅ ያለመውና በዛሬው ዕለት የሚካሄደው የ 5 ኪሎ ሜትር ሩጫ ውድድርም ከዚህ አንጻር የሚመዘን ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የቱሪስት መስህቦችን ለማስተዋወቅ ያለመው የ 5 ኪሎ ሜትር ሩጫ የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ አዘጋጅነት የሚካሄድ ነው፡፡  መነሻዉን ከሴቶች አደባባይ አድርጎ እስከ ሸራተን አዲሱ አስፓልት በሚዘልቀዉ በዚህ ሩጫ ላይ በኮሪደር ልማት የተሰሩ መዝናኛዎችን፣ ፓርኮች እና ሙዚየሞችን የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ማርኬቲንግ እና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር ፍሬህይወት ገብረመድን ገልፀዋል።

ከ1 ሺህ እስከ 1 ሺህ 5 መቶ የሚሆኑ ሰዎች እንደሚሳተፉበት በሚጠበቀው የሩጫ ውድድር፣ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ለሚወጡ አሸናፊዎች እንደየ ደረጃቸዉ ከ30 እስከ 20 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት እንደሚበረከትላቸዉ የአፍላንድ የምሽት ሩጫ ጀነራል ማናጀር አርቲስት ኢሳያስ መለሰ ጠቁመዋል፡፡ “እኔም አሻራዬን ላኑር” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው የምሽት ሩጫ የመዲናዋን የልማት ስራዎች እና የመስህብ መዳረሻዎች በስፋት ያሳያል ተብሏል። ሩጫዉ ዛሬ ግንቦት 30 ቀን ከምሽቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል ተብሏል።

አዲስ አበባ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በተሰሩና እየተሰሩ ባሉ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ ፓርኮች፣ አደባባዮችና ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መልኳ እየተቀየረ መጥቷል፡፡ በዚህ ረገድ ከአራት ዓመታት ወዲህ የተሰሩ ስራዎች ለስፖርቱ ቤተሰብና አካል ብቃት እንቅስቃሴ የማድረግ ልምድ ላላቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች ይዞት የመጣው ገጸ በረከት ቀላል አይደለም፡፡

ማህበረሰብ አቀፍ የስፖርት እንቅስቃሴውን ለጤናማ ማህበረሰብ ከመፍጠሪያነት ባለፈ ለሁሉም የስፖርት አይነቶች ሁሉ ምንጭነት እንደሚጠቅም ባለሙያዎች ያስረዳሉ። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አሰልጣኙ ዳንኤል ሙሉጌታም እንደሚገልጸው የስፖርት እንቅስቃሴውን ማህበረሰቡ ባህል እንዲያደርገው ምቹ መስሪያ ቦታዎች መስፋፋት እንደሚኖርባቸውና በዚህ ረገድ አዲስ አበባ እየሰራች ያለው ስራ የሚበረታታ ስለመሆኑ ያነሳል፡፡ የማህበረሰብ አቀፍ ስፖርትን በማጠናከር ለሁሉም የስፖርት አይነቶች ተወዳዳሪዎች ምንጭ መሆን በሚችልበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ጨምሮ ገልጿል፡፡

በእርግጥ አዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ታላላቅ ስፖርታዊ ውድድሮች እየተከናወኑባት ያለች መዲና ሆናለች፡፡ ለማሳያ ያህል ጥቂቶቹን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በየጊዜው ከሚያካሂዳቸው የማስ ስፖርት እንቅስቃሴ በተጨማሪ ከ14 ክለቦች የተውጣጡ 330 ተወዳዳሪዎች በሁለቱም ጾታ የተሳተፉበት ማራቶን ውድድር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ብስክሌት ፌዴሬሽን ከኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ሼር ካምፓኒ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የብስክሌት ውድድር እንደዚሁም ከቸርቸል ጎዳና እስከ ለገሀር በተሰራው የኮሪደር ልማት  የተከናወነው ዓመታዊ የኮካ ኮላ የብስክሌት ውድድር ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የማህበረሰብ አቀፍ ስፖርት ማስፋፊያና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ እንግዳወርቅ ዳንኤልም ከዚህ ቀደም ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት ከተማዋ አሁን ላይ በቀንም ይሁን ምሽት ላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚዘወተርባት ከተማ ሆናለች፡፡ ይህ ደግሞ ለማህበራዊ ትስስር፤ ለጤና እና ትውልድን ከመገንባት እና በስነ-ምግባር የታነጸ ዜጋ ከመፍጠር አንጻር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡ ማስ ስፖርት ለጤና ከሚሰጠው ጠቀሜታ ባሻገር በህዝቦች መካከል መቀራረብንና ወዳጅነትን በመፍጠር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተሰሩ ስራዎችም ሰፋፊ ስፖርታዊ ሁነቶችንና ውድድሮችን ለማዘጋጀት አዲስ አበባም ምሽት ላይ ጭምር ብርሃናማ የሆነችና የተስተካከለች ከተማ እየሆነች ስለመምጣቷ ያስረዳሉ፡፡

በከተማዋ ልዩ ቀለም ያለው ለሩጫ ብቻ ተብሎ በተዘጋጀው በርካታ ኪሎ ሜትሮችን በሚሸፍነው መንገድ ላይ የውጭ ሀገር ዜጎችን ጨምሮ በርካታ የመዲናዋ ነዋሪዎች በየቀኑ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ሲያደርጉ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ከእንደዚህ አይነት ዘወትርአዊ እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ ዛሬ እንደሚካሄደው አይነት የምሽት የማራቶን ስፖርታዊ ውድድሮች ከተማዋ ያላትን የቱሪዝም አቅም ከማስተዋወቃቸው በተጨማሪ መዲናዋ በምሽት ስላላት ድባብና እንቅስቃሴ ለማስተዋወቅ በር ይከፍታል ይላሉ  የምሽት ሩጫ ጀነራል ማናጀር አርቲስት ኢሳያስ መለሰ፡፡

ስፖርት ቱሪዝም ማለት የስፖርት ውድድሮችን /ዝግጅቶችን/ ለመመልከት ወይም በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ወደ አንድ የዝግጅት መዳረሻ መሄድ ነው፡፡ ይኽም በተለያዩ የስፖርታዊ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ወይም ለመመልከት መሔድን ጨምሮ፣ የስፖርት ሙዚየሞችን፣ ስታዲየሞችና ሌሎች ልማቶችን መጎብኘትን ሁሉ ያጠቃልላል። በአላይድ የገበያ ጥናት /Allied Market Research/ ሪፖርት መሰረት የዓለም ስፖርት ቱሪዝም ኢንደስትሪ ከሶስት ዓመት በፊት በወጣ መረጃ 323 ነጥብ 42 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር፡፡ በ2030 ደግሞ 1 ነጥብ 8 ትሪሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ ተገምቷል፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review