የአዲስ አበባ ዘመናዊ የከተማ ልማት ስትራቴጂዎች የነገዋን ኢትዮጵያ የሚቀርጹ ናቸው

AMN- ነሐሴ 6/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባን ለኑሮ ምቹ፣ ለጎብኚዎች ማራኪ እና ለኢንቨስትመንት ተወዳዳሪ ለማድረግ የተዘረጉት ዘመናዊ የከተማ ልማት ስትራቴጂዎች የመዲናዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የዜጎችን ሕይወት እያዘመኑ ይገኛሉ።

ቀደም ሲል ለጤና አደጋና ለቆሻሻ ተጋላጭ የነበሩ የወንዝ ዳርቻዎችን ጨምሮ የተከናወኑት የመሰረተ ልማት ስራዎች፣ ከተማዋን ማስዋብ ብቻ ሳይሆን ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እና የስራ እድል እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡

የዘመናዊ ከተማ ዋና መለኪያ ሰዎች በምቾት የሚንቀሳቀሱበት፣ የሚዝናኑበት እና የሚኖሩበት ምቹ አካባቢ መፍጠር ነው።

በዚህ ረገድ ከእንጦጦ እስከ ቀበና የተዘረጋው የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ ቀደም ሲል ለቆሻሻና ለተለያዩ የጤና አደጋዎች ተጋላጭ የነበሩ አካባቢዎችን ወደ ለምለም አረንጓዴ ስፍራዎች ቀይሯል።

በተጨማሪም የአካባቢ ጥበቃን ከኢኮኖሚ እድገት ጋር አስተሳስሮ ማሳየት እንደሚቻል በተግባር አረጋግጧል።

የአዲስ አበባ ዘመናዊ ከተሜነት በውበቷ ብቻ ሳይሆን በሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴዎቿ የሚለካ ነው፡፡

በከተማዋ የተገነቡ ፕሮጀክቶች የከተማ ቱሪዝምን ያነቃቁ ሲሆን፣ ለምሳሌ ወዳጅነት ፓርክ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማስገኘት ችሏል።

ፕሮጀክቶቹ በርካታ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ የስራ እድሎችን ከመፍጠራቸው ባለፈ፣ የአቅም ግንባታና የእውቀት ሽግግር እንዲፋጠንም አድርገዋል።

የዲጂታል መንግስት አገልግሎቶች፣ የንግድ እንቅስቃሴ፣ ፈጣን የመጓጓዣ አማራጮች እና የኢንቨስትመንት ምቹነት የዚሁ ዘመናዊ ስትራቴጂ ውጤቶች ናቸው።

ይህ በአዲስ አበባ የተጀመረው የልማት ስራ አሁን ላይ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች እየተስፋፋ ይገኛል፡፡

ይህም ከተሞች የራሳቸውን ልማት ብቻ ከመከታተል ይልቅ በንግድ፣ በቱሪዝም፣ በሎጅስቲክስ እና በኢንዱስትሪ እንዲተሳሰሩ እድል ፈጥሯል።

የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት መሠረተ ልማትን በመሳብ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተወዳዳሪነት ያጠናክራል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ(ዶ/ር) እንዳመለከቱት፣ በስርዓት የታቀዱ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች በከተማ ልማት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ከመሆናቸውም በላይ ሰዎችን በበጎ ዓላማ እንዴት ማቀናጀት እንደሚችሉ በተግባር እያረጋገጡ ይገኛሉ።

በአሁኑ ወቅት እየተከናወኑ ያሉ ቀጣይነት ያላቸው፣ አረንጓዴ እና ለሁሉም ተደራሽ የሆኑ የከተማ ልማት ስራዎች የዛሬውን ችግር መፍታት ብቻ ሳይሆን፣ ለነገዋ ኢትዮጵያ የከተማ መዋቅር መሠረት የሚጥሉ ስልታዊ ኢንቨስትመንቶች ናቸው።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review