ሀገራዊ ምክክር ጉባዔው የጋራ መግባባትን የሚያጠናክርና የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት የሚያስችል ታሪካዊ ድልድይ ነው – ተመካካሪዎች

AMN- ነሐሴ 6/2018 ዓ.ም

ሀገራዊ ምክክር ጉባዔው የጋራ መግባባትን የሚያጠናክር እና የተሻለች፣ ሰላሟ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን መገንባት የሚያስችል ታሪካዊ ድልድይ መሆኑን ተመካካሪዎች ገለጹ፡፡

የምክክር ጉባኤው ለኢትዮጵያ ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑን ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉ ተመካካሪዎች ተናግረዋል፡፡

የምክክሩ ተሳታፊ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ፤ በመከባበር መኖር እንዲሁም በጋራ ያሉ ልዩነቶች ላይ ተነጋግሮ መፍትሄ ማምጣት አስፈላጊ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡

ብዝሃ ማንነት ባለባት ሃገር ባለመነጋገር እና በግል ፍላጎት ከሄድን ሃገርን መጎተት ነው የሚሆነው የሚሉት ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ፤ በዚህም ተነጋግረንና ተዋውቀን ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መወሰን ይገባል ብለዋል፡፡

ሌላኛው የምክክሩ ተሳታፊ ወጣት ወንድማገኝ ገርሶ፤ ኢትዮጵያ ለብዙ ዓመታት ብዙ ችግሮችን ተጋፍጣ እዚህ መድረሷን በመግለጽ ችግሮችን ለመፍታት የምክክር ጉባዔው ጠቃሚ ነው ብሏል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭቶች እንደነበሩ በማንሳት ግጭቶችን ለማስቀረትም እየተካሄደ ባለው ምክክር ተሳታፊዎች በመከባበር ሀሳባቸውን በነፃነት እያቀረቡ መሆኑን ገልጿል፡፡

በቀጣይም ሰላሟ የተረጋገጠ፣ያደገች፣ የለማች፣ ህዝቦቿ በጋራ በፍቅር የሚኖሩባትን ኢትዮጵያ እጠብቃለሁ ብሏል።

የምክክሩ ተሳታፊ ሜሪ ደስታ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን የሚያስቀጥሉበት ሁኔታ ይፈጠራል የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቅሰው የሚያግባቡን ነገሮች በርካታ በመሆናቸው እየተካሄደ ያለው ሃገራዊ ምክክር ስኬታማ በሆነ መልኩ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

እንዲሁም ወጣት ቢኒያም ትዕግስቱ፤ ምክክሩ ወሳኝ ምእራፍ ላይ መድረሱን እንዲሁም ሁሉንም ያካተተ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ተመካካሪዎቹ ምክክሩ የነገዋን ኢትዮጵያ ሊገነባ በሚችል መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው ጉባዔው በውይይት እያደገ እና እየጎለበተ የመጣ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review