የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የተጠናከረ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከመላው ኢትዮጵያ ከተወጣጡ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተለያዩ አጀንዳዎች ያሉ አለመግባባቶችን ለመፍታት ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ምክክር እንዲኖር ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በሀገራዊ ምክክሩ በርካታ የህብረተሰብ ክፍል እየተሳተፈ እንደሚገኝ ጠቅሰው ፓርቲዎችም ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ይሁንና አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክክሩ ላይ ተሳትፎ እያደረጉ እንደማይገኝ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲዎቹ ሀሳባቸውን እንዳያነሱ የሚከለክል ነገር እንደሌለ አንስተዋል።
ሁሉም የፓለቲካ ፓርቲዎች የሀሳብ ልዕልናን መሰረት በማድረግ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ አንድ የፖለቲካ መድረክ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲዎች ያላቸውን ሀሳብ እንዲያነሱ ጠይቀዋል።
በምክክሩ ላይ በርካታ አጀንዳዎች እየተነሱ መሆናቸውን ጠቅሰው ምክክሩ በውይይት እና በንግግር ለሚያምን አካል በሙሉ ክፍት ነው ብለዋል።
በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የሚነሱ ሀሳቦች ተለይተው ህግን መሰረት ባደረገ ሁኔታ ማሻሻያ እንደሚደረግባቸው ተናግረዋል።