AMN- ሐምሌ 10/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር፣ አዲስ ፈቃድ ላወጡ አስመጪዎች እና ላኪዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሒሳብ ቁጥር አሰጣጥን የሚያቀል አዲስ የዲጂታል አገልግሎት አስተዋውቋል።
ይህ አገልግሎት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሒሳብ ቁጥሮች በጉምሩክ ኮሚሽን አንድ መስኮት አገልግሎት (Customs Electronic Single Window – eSW) በኩል ያለምንም ውጣ ውረድ እንዲሰጥ በማስቻል፣ አስተዳደራዊ ሂደቶችን የሚቀንስ እና ፈጣን የንግድ አሠራርን የሚደግፍ መሆኑን የብሔራዊ ባንክ ገልጿል።
አዲሱ አገልግሎት የሚመለከተው ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሒሳብ ቁጥር ለሚያወጡ እና አዲስ ፈቃድ ላገኙ አስመጪዎች እና ላኪዎች ብቻ ነው።
ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሒሳብ ቁጥር ያላቸው የንግድ ተቋማት ለሁሉም የገቢ እና የወጪ ንግድ ግብይቶቻቸው ይጠቀሙበት በነበረው ነባር ቁጥር መጠቀም እንደሚችሉ ከብሔራዊ ባንክ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ይህ አሠራር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገቢ እና የወጪ ንግድ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን ለማዘመን፣ የንግድ አሠራርን ምቹ ለማድረግ፣ እንዲሁም የዲጂታል የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥን ለማጠናከር እያከናወነ ያለው ቀጣይ ጥረት አካል ነው።