ኢትዮጵያ የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ አገራት ድርጅት ሊቀመንበር ሆና ተመረጠች

You are currently viewing ኢትዮጵያ የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ አገራት ድርጅት ሊቀመንበር ሆና ተመረጠች

AMN – ሐምሌ 10/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ አገራት ድርጅት ሊቀመንበር ሆና መመረጧን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

121ኛው የአካፓድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ሐምሌ 8-9 ቀን 2018 ዓ.ም. ቤልጅየም መዲና ብራስልስ ተካሂዷል።

በጉባኤው ላይ በገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው የተመራ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎችን ያካተተ የልኡካን ቡድን ኢትዮጵያን በመወከል ተሳትፏል።

የሚኒስትሮቹ ስብሰባ የማላቦ ዲክላሬሽን አተገባበር ሂደትን ፣ የድርጅቱን የፋይናንስ አቅም በዘላቂነት ለመገንባት ስለሚወሰዱ እርምጃዎች ፣ የድርጅቱ ማሻሻያ ሂደት ያለበትን ደረጃ ፣ የሳሞአ ስምምነትን የትግበራ ሂደት እንዲሁም ሌሎች የድርጅቱንና የአባል ሀገራትን ጥቅም ስለሚያስጠብቁ ጉዳዮች ውይይት አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያ አቋሟን የሚያንጸባርቁ እና ድርጅቱን በፕሬዚዳንትነት በምትመራበት ወቅት የምትከተላቸውን የትኩረት አቅጣጫዎች የሚያመለክቱ ንግግሮች አቅርባለች።

በጉባኤው ማጠናቀቂያም ኢትዮጵያ ከኦገስት 1 ቀን 2026 እስከ ጃንዋሪ 31 ቀን 2027 የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓስፊክ አገራት ድርጅት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆና መመረጧን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

ኢትዮጵያ በቀጣይ ስድስት ወራት የጉባኤው ሰብሳቢነቷ ወቅት ቅድሚያ የምትሰጣቸውን የትኩረት ጉዳዮች አስተዋውቃለች፡፡

የድርጅቱን ጽ/ቤትና የአባል አገራትን የፖሊሲ ነጻነት ማረጋገጥ፣ በራስ አቅም ሊከናወኑ ስለሚችሉ የልማት ስራዎችና የአገር ውስጥ ሃብት ማሰባሰብ የኢትዮጵያን ተሞክሮ በማጋራት በምሳሌነት መምራት፣ በተቋሙ ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲጠናከር በማድረግ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲወገድ መስራት፣ የድርጅቱ የፋይናንስ እጥረት በዘላቂነት እንዲፈታ የተጀመረው የሀብት ማሰባሰብ ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ እና የአውሮፓ ህብረት እና የአካፓድ ግንኙነት መሠረት የሆነው የሳሞአ ስምምነት አፈጻጸም በተሻለ መልኩ እንዲጓዝ መስራት ኢትዮጵያ ያስተዋወቀቻቸው የትኩረት ጉዳዮች ናቸው።

ኢትዮጵያ ድርጅቱ ከተመሰረተ እ.ኤ.አ. 1975 ጀምሮ ሁለት ጊዜ (እ.ኤ.አ. ከነሀሴ 1 ቀን 1986 እስከ ጥር 31 ቀን 1987 እና ከየካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. እስከ ሀምሌ 31 ቀን 2017 ) ተቋሙን በሰብሳቢነት አገልግላለች።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የአካፓድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሆና መመረጧ፣ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን የዲፕሎማሲ ተፅዕኖ ፈጣሪነት በድጋሚ የሚያረጋግጥ ታላቅ ስኬት ነው።

ታሪካዊው ኃላፊንት ኢትዮጵያ በደቡብ-ደቡብ ሁለንተናዊ ትብብር ላይ ያላትን ተሳትፎ ይበልጥ ከማጠናከሩ ባሻገር፣ ከአባል አገራቱና ከአውሮፓ ህብረት ጋር የሚደረጉ ትብብሮችን በበላይነት ለመምራት፣ ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበር እና መልካም ገፅታዋን ለመገንባት የዲፕሎማሲ ዕድሎችን እንደሚከፍት ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ለኖቬምበር 2026 ዓ.ም. የታቀደው የ122ኛው የአካፓድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት አዲስ አበባ እንዲካሄድ በድርጅቱ አባል ሀገራት ተወስኖ ጉባኤው መጠናቀቁን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review