የሀገራዊ ምክክሩ የንዑስ ቡድኖች ውይይት በይፋ ተጀመረ

You are currently viewing የሀገራዊ ምክክሩ የንዑስ ቡድኖች ውይይት በይፋ ተጀመረ

AMN- ሐምሌ 13/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር የሀገራዊ ምክክር ጉባኤውን አሁናዊ ሂደት አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫውም ተመካካሪዎች ዛሬ ሐምሌ 13 ቀን በንዑስ ቡድኖች ተከፋፍለው በተመደቡባቸው አጀንዳዎች ላይ መመካከር ጀምረዋል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ፤ ለእያንዳንዱ አጀንዳ 500 ተመካካሪዎችን ያካተተ ዐቢይ የሥራ ቡድን ተደራጅቷል።

እያንዳንዱ ዐቢይ ቡድን ደግሞ 50 ተመካካሪዎች ያሉባቸው 10 ንዑስ ቡድኖችን የያዘ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 80 ንዑስ ቡድኖች በተመደቡላቸው አጀንዳዎች ላይ ውይይት እያካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ተመካካሪዎቹ በኮሚሽኑ ይፋ በተደረጉት ስምንት አጀንዳዎች ላይ ተመድበው ቅድመ ምክክር ውይይቶችን፣ ትውውቆችን እና በምክክሩ የአሠራር ሥርዓቶች ላይ ግንዛቤ ሲወስዱ መቆየታቸውንም አስታውቀዋል።

ኮሚሽነሩ እንደገለጹት፣ ዛሬ የተጀመረው የንዑስ ቡድን ውይይት የሀገራዊ ምክክሩ ቁልፍ ምዕራፍ ሲሆን፣ ተመካካሪዎች በተመደቡባቸው አጀንዳዎች ላይ ሐሳባቸውን የሚያቀርቡበትና አንዱ የሌላውን ሐሳብ በማዳመጥ የሚመካከሩበት ሂደት መሆኑን ጠቁመዋል።

የውይይቱን ሂደት ለማስተባበር ኮሚሽኑ በሥራ ልምድና በትምህርት ዝግጅት ብቃት ያላቸው 160 አመካካሪዎች እና 256 የቃለ ጉባኤ ጸሐፊዎች የምክክሩን ሂደት በመመዝገብና በመደገፍ እየሠሩ መሆኑን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review