ተመራቂዎች ሥራ ጠባቂ ሳይሆን ሥራ ፈጣሪ በመሆን ከራሳቸው አልፈው ሳይደላው ከራሱ ቀንሶ እና ተቸግሮ ላስተማራቸው ቤተሰብ፣ ለመላው ህዝብና ለሀገራቸው ሁለንተናዊ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር) አሳስበዋል፡፡
ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ባለሙያዎችንና አመራሮችን ለማፍራት የጀመረውን አዲስ ምዕራፍ በተለያዩ አዳዲስ ስነዘዴዎች በመታገዝ ለትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ተግባራትን ከመስራት በተጓዳኝ፣ የተሰጠውን በጀት አቅም በፈቀደ ጥረት ሁሉ አብቃቅቶ በመጠቀም ተማሪዎችን በእውቀትና በክህሎት ቀርፆ፣ በመልካም ሰብዕና እና ስነምግባር ኮትኩቶ ለዛሬዋ ቀን አድርሷል ብለዋል፡፡
ተመራቂዎች ከዩኒቨርሲቲው የቀሰሙትን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም መላውን ህዝባቸውን በታማኝነት እና በቅንነት እንዲያገለግሉም አሳስበዋል፡፡
በማደግ ላይ ባለች ሀገር ውስጥ እንደሚገኝ ተመራቂ፣ ከምረቃ በኋላ የሚኖራችሁ ጉዞ አልጋ ባልጋ እንደማይሆን እንገነዘባለን ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
ውስን ሀብቶች ባሉባት፣ በተቃራኒው ደግሞ ፍላጎቶች እየጨመሩ በሚሄዱበት አውድ ውስጥ ጉዟችሁ አቀበት ቁልቁለት እንደሚኖረው እንረዳለን ሲሉም አክለዋል፡፡
ነገር ግን የማይናወጥ ጽናት፣ ዓላማ እና ቁርጠኝነት ዋና ዋናዎቹ የአንድ የትምህርት ባለሙያ ሀብቶች በመሆናቸው ተግዳሮቶችን ሁሉ በብልሀትና በጽናት አልፋችሁ አደራችሁን እንደምትወጡ አንጠራጠርም በማለት ያላቸውን ፅኑ እምነት ገልጸዋል፡፡
በምትሄዱበት ችግሯን የምታወሩ ሳይሆን ችግሯን የምትቀርፉ፣ በምክንያት የምታምኑ፣ አስለቃሽ ሳይሆን እምባ አባሽ በመሆን ሀገር ወዳድ ትውልድን በዕውቀት የምትወልዱ እንድትሆኑ መርቀን ወደ ትውልድ ከአደራ ጋር እየላክናችሁ ነው ብለዋል፡፡
በታምራት ቢሻው