የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ጋር በማስተሳሰር በስፋት እየተከናወነ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሃይ ጳውሎስ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በየካ ተራራ በመገኘት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አመራር አባላት እና ሰራተኞች ጋር የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩም ቀደም ብሎ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በተዘጋጀ ስፋራ ላይ ተከናውኗል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሃይ ጳውሎስ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ዜጎች እየተሳተፉ ናቸው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሰራተኞችና አመራር አባላትም በመርሃ ግብሩ እየተሳተፉ መሆኑን አንስተው፤ የጽህፈት ቤቱ ሰራተኞች በመርሃ ግብሩ 100ሺህ ችግኞችን የመትከል እቅድ መያዛቸውን ተናግረዋል።
የዛሬው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በተከነወኑባቸውና ከዚህ ቀደም በባህር ዛፍ ተሸፍነው በነበሩ ስፍራዎች የተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
የጽህፈት ቤቱ ሰራተኞች ዛሬ የተከሉትን ጨምሮ የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ጋር በማስተሳሰር በስፋት እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ የተሳተፉት የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በበጋ ወቅት ሲከናወኑ የቆዩት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ጋር በስፋት እንዲተሳሰሩ መደረጉን ጠቁመዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መከናወኑን አንስተው፤ ከዚህም ውስጥ ወደ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር በሚጠጋው መሬት ላይ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እንደሚከናወን መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የዛሬ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብረም ይህንን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሃይ ጳውሎስ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከዛሬ ባሻገር የነገ ትውልድ ስንቅ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ ሁሉም ዜጋ በየአካባቢው በመርሃ ግብሩ በንቃት በመሳተፍ አሻራውን እንዲያኖር ጥሪ አቅርበዋል።
“በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሃሳብ እየተከናወነ ባለው የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞች ይተከላሉ።