AMN- ሚያዝያ 23/2018 ዓ.ም
ዓለም አቀፍ የሰራተኞች ቀን፣ በተለምዶ “ሜይ ዴይ” ተብሎ የሚጠራው፣ የላብ አደሩን እንቅስቃሴና ሠራተኞች የታገሉለትን ህጋዊ መብቶች ለማክበር የሚታሰብ ቀን ነው።
ዘመናዊው የሜይ ዴይ አመጣጥ ከኢንዱስትሪ አብዮት በኋላ የሠራተኛውን የሥራ ሰዓት ደረጃ ለማስያዝ ከተደረገው ትግል ጋር የተያያዘ ነው።
እ.ኤ.አ ግንቦት 1 (ሜይ 1) መነሻ በቺካጎ፣ አሜሪካ ሄይማርኬት በተሰኘ አደባባይ የተከሰተ ክስተት ነው። በወቅቱ የኢንዱስትሪ ሠራተኞች በቀን ውስጥ ከ10 እስከ 16 ሰዓታት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይሰሩ ነበር።
የሠራተኛ ማህበራት “ከግንቦት 1 ቀን 1886 ጀምሮ አንድ የሥራ ቀን 8 ሰዓት መሆን አለበት” የሚል ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ይህ ጥያቄ ተጠናክሮ ቀጥሎ እ.አ.አ. በ1889 በፓሪስ የተካሄደው የዓለም አቀፍ የሶሻሊስት ድርጅቶች ስብሰባ ላይ ግንቦት 1 ቀን የዓለም ሠራተኞች ቀን ሆኖ እንዲከበር ወሰነ።
እ.አ.አ. ከ1891 ጀምሮ ቀኑ በይፋ መከበር የጀመረ ሲሆን፣ በአውሮፓ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በእስያና በአፍሪካ ተስፋፍቶ በብዙ ሀገራት ብሔራዊ በዓል ሆኗል።
ይህ ቀን በታሪክ ውስጥ ለተገኙ በርካታ የሠራተኛ መብት ድሎች እንደ ምልክት ይታያል፡፡
በዚህም “8 ሰዓት ለሥራ፣ 8 ሰዓት ለእረፍት፣ 8 ሰዓት ለግል ጉዳይ” የሚለውን መርህ ማረጋገጥ፣ በሥራ ቦታ የሚደርሱ አደጋዎችንና ህመሞችን ለመከላከል ህጎች መውጣት ችለዋል፡፡
ህፃናት በአደገኛ የኢንዱስትሪ ሥራዎች ላይ እንዳይሰማሩ መከልከል እና ሠራተኛው በዝቅተኛ ደሞዝ እንዳይበዘበዝ ጥበቃ እንዲያገኝ ህጋዊ መሠረት መወሰን የተገኙ ዋና ዋና ስኬቶች ናቸው።
ይሁን እንጂ አስገራሚው ነገር፣ እንቅስቃሴው በአሜሪካ ቢጀመርም፣ አሜሪካ “የሰራተኞች ቀንን” የምታከብረው በመስከረም ወር የመጀመሪያው ሰኞ ላይ ነው።
በወቅቱ የነበሩት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ግሮቨር ክሊቭላንድ፣ በዓሉ ግንቦት 1 ቀን መከበሩ አላስፈላጊ አስተሳሰቦችን ሊያነሳሳ ይችላል በሚል ፍራቻ፣ ቀኑን ወደ መስከረም ወር እንዲቀየር ማድረጋቸው ይነገራል።
በአሁኑ ጊዜ የሰራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) ለሁለት ዋና ዋና ዓላማዎች የሚውል ሲሆን፣ ይህም ሠራተኞች ለሰው ልጅ ስልጣኔና ለኢኮኖሚ እድገት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ለማክበር ነው፡፡
እንዲሁም የሠራተኛ ማህበራት ስለ ወቅታዊ ጉዳዮች፣ እንደ የኑሮ ውድነት፣ ፍትሃዊ ደመወዝ እና የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በሥራ ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ለመሳሰሉት ድምፃቸውን የሚያሰሙበት ቀን ነው፡፡
በታምራት ቢሻው