በሐረር ለሚገነባው ሞዴል የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ከ540 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡ ተገለፀ

You are currently viewing በሐረር ለሚገነባው ሞዴል የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ከ540 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡ ተገለፀ

AMN – መስከረም 9/2018 ዓ.ም

በሐረር ለሚገነባው ሞዴል የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ከ540 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገልፀዋል፡፡

በሐረር ሞዴል የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ተጀምሯል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እና የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ በክልሉ የሐረር ሁለተኛ ደረጃ ሞዴል ትምህርት ቤት ግንባታን አስጀምረዋል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፤ በክልሉ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማስፋት ባለፉት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተው በዚህም ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ተናግረዋል። ግንባታው የተጀመረው ሞዴል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን አንስተው የክልሉን የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት በማሳደግ ረገድ ፋይዳው የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።

የአካባቢውን ልማትና እድገት ለማጎልበት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ጠቁመው፤ ለሞዴል ትምህርት ቤቱ ግንባታ መጀመርም ትምህርት ሚኒስቴርን ማመስገናቸውን ኢዜአ ዘግቧል። የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም በሐረር የሚገነባው ሞዴል ትምህርት ቤትም የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን አንስተው በዘመናዊ ትምህርት የታነፀና በእውቀት የበለጸገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ የማፍራቱ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

መንግስት በክልሉ ለሚገነባው ሞዴል ትምህርት ቤት ከ540 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን ጠቅሰው ግንባታው በተያዘለት ጊዜ በጥራትና በፍጥነት ተገንብቶ የሚጠናቀቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ጌቱ ነገዎ፤ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ውጤት እያመጡ መሆኑን አንስተው በዚህ ረገድ የሞዴል ትምህርት ቤቱ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review