እያደገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና ህዝብ የባህር በር ጥያቄ ለማንሳት የሚሸማቀቅበት ጊዜ ማብቃቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የባሕር በር ጥያቄን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ነው።
የኢትዮጵያ በቀይ ባሕር የመጠቀም ጉዳይ አይቀሬ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ከልክ ያለፈ ራስ ወዳድነት ለጉርብትና እንደማይጠቅም አመላክተዋል።
ሁሉም ሀገር የብሔራዊ ደህንነት ስጋት እና የብሔራዊ ጥቅም ጥያቄ እንዳለበት አመላክተው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም የኢፍትሀዊነት ተጠቂ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም፣ መንግስት ቀይ ባህር የኢትዮጵያ ህጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ነው ብሎ ያምናል፤ ይህንንም ለማሳካት ለሰላም ቅድሚያ ይሰጣል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ባለቤት ለመሆን የያዘችው ዕቅድ እንዲሳካ አሜሪካ ቻይና፣ ሩስያ እና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ለተለያዩ አካላት በተገቢው ልክ ማስረዳቷን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
አሁንም ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ እና በድርድር ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ ዝግጁ መሆኗን አጽንዖት ሰጥተዋል።
ነገር ግን ቀይ ባህርን ለማጣት 30 አመታት እንደወሰደብን ሁሉ ባህሩን ድጋሚ ለመጠቀም 30 አመታትን አንጠብቅም ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዳዊት በሪሁን