የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ የሀገራቱን 55ኛ ዓመት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አስመልክቶ የደስታ መግለጫ መልዕክት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) አስተላልፈዋል።
ዋንግ ዪ በመልዕክታቸው ቻይና እና ኢትዮጵያ ጥልቅ እና ለረጅም ጊዜ የቆየ ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጸው ግንኙነታቸው በዓመታት መካከል ፀንቶ መቀጠሉን አመልክተዋል።
ባለፉት 55 ዓመታት ሁለቱ ሀገራት የነበራቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመልካም እምነት ላይ እና በአስፈላጊ ጊዜ እርስ በእርስ በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ መሆኑን አመልክተዋል።
ወዳጅነቱ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት አጋርነት እና ትብብር ማሳያ ነው ብለዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራቱ መሪዎች ስትራቴጂካዊ መሪነት የሁለትዮሽ ትብብሩ የበለጠ እየጠነከረ መምጣቱን አመልክተዋል።
ከምንጊዜውም በላይ የዳበረው የፖለቲካ የጋራ መተማመን እና ፍሬያማ ተግባራዊ ትብብር መገለጫው የሆነው የሁለትዮሽ ግንኙነት ለሀገራቱ ህዝቦች ተጨባጭ ውጤቶችን ማስገኘቱን ነው ያብራሩት።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የ55ኛ ዓመቱን የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በዓል እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም (ፎካክ) ጉባኤ ውጤቶች እና የሀገራቱ መሪዎች የጋራ መግባባት ላይ የደረሱባቸውን ጉዳዮች ለመተግበር እንዲሁም ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂክ አጋርነት (all-weather strategic partnership) የበለጠ ለማጠናከር ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
በሁኔታዎች የማይለዋወጥ የጋራ ራዕይን ማዕከል ያደረገ የቻይና-አፍሪካ ማህበረሰብ አዲስ የትብብር ምዕራፍ የመክፈት ስራ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1970 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።