AMN ሐምሌ 21/2018 ዓ.ም

በብልፅግና ፓርቲ ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ጎብኝቷል።
ልዑኩ በጉብኝቱ ወቅት የሳኔቴ አምባን፣ 4 ሺህ 377 ሜትር ከፍታ ያለውን የቱሉ ዲምቱ ተራራ እና የዲንሾ ፓርክን በመጎብኘት የአካባቢውን ልዩ የተፈጥሮ ሀብትና የቱሪዝም እምቅ አቅም ተመልክቷል።

ቢቂላ ሁሪሳ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ፀጋዎች የበለጸገች ሀገር ብትሆንም እነዚህን ፀጋዎች በአግባቡ በማልማትና ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ገና ብዙ የሚሰራ ሥራ እንዳለ ተናግረዋል።

መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፍ በሚሰጠው ልዩ ትኩረት በመላ ሀገሪቱ የቱሪዝም ልማት እየተፋጠነ መሆኑን ጠቅሰው፣ እንደ ባሌ ያሉ በተፈጥሮ ፀጋ የታደሉ አካባቢዎችን በአግባቡ ማልማትና በሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ሥራዎች ለዓለም ማስተዋወቅ ለሀገራዊ ብልፅግና ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አመልክተዋል።

ይህ ጉብኝት የተካሄደው የብልፅግና ፓርቲ ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2019 በጀት ዓመት ዋና ዋና ዕቅዶች የሚገመገሙበት መድረክ ከዛሬ ጀምሮ በባሌ ሮቤ ከተማ ከመካሄዱ አስቀድሞ ነው።

መድረኩ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፣ የዘርፉ ከፍተኛ አመራሮችና ከሁሉም ክልሎች እንዲሁም ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች አመራሮች መሳተፋቸዉን ከፓርቲዉ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡