ለዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ መግባባት መሰረት እየጣለ የሚገኘው ታሪካዊው የምክክር ጉባዔ

AMN- ሐምሌ 21/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ለዘመናት ስር የሰደዱና ለተለያዩ አለመግባባቶች ምክንያት የሆኑ ሀገራዊ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድና በጋራ መግባባት ለመፍታት የታለመው ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጉባዔ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

በመዲናችን አዲስ አበባ ከመላው ሀገሪቱ የተወጣጡ ተመካካሪዎች በተገኙበት እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ ጉባዔ፤ ተሳታፊዎች በስምንት ዋና ዋና ጉዳዮችና በበርካታ ንዑሳን አጀንዳዎች ላይ ሰፊ ውይይት እያደረጉ ነው።

የጉባዔው ተሳታፊዎች ለኤ ኤም ኤን እንደገለጹት፣ የምክክር መድረኩ እያንዳንዱ ተሳታፊ ሀሳቡን ያለ ምንም ስጋትና ገደብ በነፃነት የሚያንጸባርቅበት መሆኑን እና የመደማመጥ፣ የመከባበርና የሌሎችን ሀሳብ በጸጋ የመቀበል ባህል ጎልቶ እየታየበት መሆኑን አስረድተዋል።

በመድረኩ የሚነሱ ሀሳቦችና አስተያየቶች የሀገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚቀርጹ እንደሆኑም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የጉባዔው ተሳታፊ የሆኑት አቶ ሃጂ ሙስጠፋ ናስር፣ በመድረኩ ላይ የታየው የእርስ በእርስ መከባበርና የመደማመጥ ባህል የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተሳታፊዎች ሀሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን በመጠቀም የወከሏቸውን አካላት ጉዳይ እና በቀጣይ መፍትሔ ሊበጅላቸው የሚገቡ ዋና ዋና አጀንዳዎችን እያነሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ወ/ሮ ዘነበች ጌታነህ በመደማመጥ፣ በመከባበርና የአንዱን ሀሳብ አንዱ በመቀበል ሂደት ውስጥ ማለፋቸውን የገለጹ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ተሳታፊ ያቀረበው ሀሳብ ሀገር ለማጽናት ያለመ በመሆኑ ውጤቱ መልካም እንደሚሆን ያላቸውን እምነት አጋርተዋል።

አክለውም የተደራጁበት የውይይት ቡድን የሁሉንም የሀገሪቱ ክፍሎች ብዝሃነት ያቀፈ በመሆኑ፣ አባላቱ እርስ በእርስ እንዲቀራረቡና አጠቃላይ የኢትዮጵያን ገጽታ በአንድነት እንዲመለከቱ ወሳኝ አጋጣሚ መፍጠሩን አስረድተዋል።

ሌላዋ የጉባዔው ተሳታፊ ወ/ሮ ጥያ ደስታ በበኩላቸው፣ ተሳታፊዎች ሂደቱን በጥሞና በመከታተልና አስፈላጊ ጥያቄዎችን በማንሳት እንዲሁም ተገቢ ምላሾችን በማግኘት ለመፍትሔው አካል መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል።

መቶ አለቃ ተስፋዬ ናትናኤልም በውይይቱ እያንዳንዱ ተሳታፊ የሚያቀርበውን ሀሳብ በጥሞና በማዳመጥ በግልጽነት እና በነፃነት መወያየት መቻሉን አረጋግጠዋል።

ከመደበኛው የአጀንዳ ውይይት ባለፈ፣ ጉባዔው ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ዜጎች እርስ በእርስ እንዲቀራረቡና እንዲተዋወቁ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል፡፡

የሃገራዊ የምክክር ጉባዔ፤ ኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቁ መዋቅራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።

በውይይቱ ላይ የታየው የመደማመጥና የመከባበር መንፈስም ጉባዔው ለሀገራዊ መግባባትና ለዘላቂ ሰላም ጠንካራ መሰረት እንደሚጥል ይታመናል።

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review