በመዲናዋ በበጀት ዓመቱ እስካሁን 62 ወላጅ አጥ ህጻናት የጉዲፈቻ ቤተሰብ አግኝተዋል

You are currently viewing በመዲናዋ በበጀት ዓመቱ እስካሁን 62 ወላጅ አጥ ህጻናት የጉዲፈቻ ቤተሰብ አግኝተዋል

AMN- ህዳር 23/2018 ዓ/ም

በበጀት ዓመቱ እስካሁን 62 ወላጅ አጥ ህጻናት የጉዲፈቻ ቤተሰብ ማግኝታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ህጻናትና ማህብራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው በተለያየ ምክንያት ወላጅ አጥ የሆኑና ለችግር የተጋላጡ ህጻናትን ደህንነት ለመጠበቅ እየሰራ እንደሚገኝ ለኤ ኤም ኤን ኤፍኤም 96.3 ሬዲዮ አስታውቋል፡፡

የአደራ ቤተሰብ፣ የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ፣ የተቆጥሮ ዝምድና ማለትም ከቤተሰብ ጋር እንዲኖሩ ማድረግን ጨምሮ የቤተሰብ አቅም ማጠናከርን የመሳሳሉ አማራጮችን በመተግበር ላይ እንደሚገኝ ነው በቢሮው የህጻናት መብት ማስጠበቅ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አንዱዓለም ታደሰ የገለጹት፡፡

በተለይም ቢሮው ወላጅ አጥ ህጸናትን ባሉት ጊዚያዊ የማሳደጊያና የማቆያ ተቋማቱ ውስጥ እየተንከባከበ እንደሚገኘ የገለጹት አቶ አንዱዓለም፣ በበጀት ዓመቱ እስካሁን ወደ 62 ህጻናት የጉዲፈቻ ቤተሰብ ማግኝታቸውን ተናግረዋል።

ይሁንና ቁጥሩ በቂ አለመሆኑን በመግለጽ፣ አሁንም በርካታ ህጻናት በማሳደጊያዎች የጉደፈቻ ቤተሰብ የሚፈልጉ መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

የሚጣሉ እንዲሁም በቤተሰብ እጦት የሚገፉ ህጻናት የሁሉም ኢትዮጵያዊ አደራ ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ለእነዚህ ህጻናት የጉዲፈቻ ቤተሰብ በመሆን ልንጠብቃቸው ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ህብረተሰቡ ያለ ጾታ፣ ቀለም እና አድሜ ገደብ ለህጻናት በጥሩ ልብ ወላጅ እንዲሆናቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የውጭ ሀገር ጉዲፈቻ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በአዋጅ መከልከሉን ተከትሎ የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡

ይህን ታሳቢ በማድረግ በአዲስ አበባ በ2007 ዓ.ም ሶስት ህጻናትን ብቻ በሀገር ውስጥ ለጉዲፈቻ በመስጠት በተጀመረው ሰራ አስካሁን ከ 1 ሺህ 600 በላይ ወላጅ የሌላቸዉ ህጻናት ወላጅ እንዲያገኙ ማስቻሉን አመላክተዋል፡፡

በረውዳ ሸምሱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review