AMN- ሰኔ 5/2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተጀመረው ታሪካዊ ጉዞ ስኬታማ ሆኖ፣ የተተለሙ ታላላቅ ሀገራዊ ግቦች እውን እንዲሆኑ ሁሉም ዜጋ ለምክክሩ ውጤታማነት የተለመደ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ኮሚሽኑ አሳስቧል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)፣ ዋናውን ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ ጉባኤው ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ሳምንታት ያህል በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ይፋ አድርገዋል።
በእስከ አሁኑ ጉዞም፣ በተለያዩ ምዕራፎች ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ማካሄድ የሚያስችል አሳታፊና አካታች የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊ ልየታ ሥራ በስኬት ተከናውኗል ብለዋል።

በሀገሪቱ ከሚገኙ 1 ሺህ 234 ወረዳዎች፣ 12ቱም ክልሎች፣ ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እና በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ዜጎች ጋር ስኬታማ የምክክር መድረኮች መካሄዳቸውንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት ብሔራዊ መግባባት መፍጠር የሚያስችል ምቹ ምህዳር መፍጠሩንም ተናግረዋል።
የእስከ አሁኑ ሂደት ፍፁም ግልጽ፣ ገለልተኛ፣ አካታችና አሳታፊነቱን ጠብቆ የተካሄደ መሆኑ መረጋገጡንም ነው ያነሱት።
ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ሳምንታት በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን፣ ተሳታፊዎች ጉባኤው ከመጀመሩ አንድ ሳምንት ቀደም ብለው ወደ ዋና ከተማዋ እንደሚገቡም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን በተወካዮቻቸው አማካኝነት ተደማምጠው በመመካከር የሚያቀርቧቸውን ምክረ-ሃሳቦች በመተግበር ሀገርን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር የሁሉንም የጋራ ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ አንስተዋል።

የተተለሙ ታላላቅ የኢትዮጵያ የዕድገት ግቦች እንዲሳኩ ሁሉም ዜጎች ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የተለመደውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በታሪካዊው የምክክር መድረክ እስከ አሁን በተለያዩ ምክንያቶች ያልተሳተፉ ወገኖች ወደ ምክክሩ እንዲቀላቀሉ የተጠየቀ ሲሆን፣ ኮሚሽኑም እነሱን ተቀብሎ ለማስተናገድ በሩ ምንጊዜም ክፍት መሆኑን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ተስፋ የጣሉበትን ታሪካዊ የምክክር ኃላፊነት በከፍተኛ ታማኝነት፣ ገለልተኝነት እና ቁርጠኝነት ለመወጣት ሙሉ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸዋል።
በታምራት ቢሻው