በአፍሪካ ሚዲያዎችን የሴቶች ተሳትፎ እና ደህንነት ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ የአፍሪካ ህብረት አስታወቀ።
በአፍሪካ ውስጥ በሚዲያ ዘርፍ የሚሰሩ ሴቶችን አስመልክቶ የተዘጋጀ ኮንፍረንስ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
“ቃልን ወደ ተግባር፤ የሚዲያ ደህንነት እና የስርዓተ ጾታ እኩልነትን የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎችን መንደፍ እና መተግበር” የኮንፍረንሱ መሪ ሀሳብ ነው።
በኮንፍረንሱ ከመላው አፍሪካ የተውጣጡ ጋዜጠኞች፣ ፖሊሲ አውጪዎች እና የሚዲያ ተቆጣጣሪዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት፣ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችና ምሁራን ይሳተፋሉ።

ደህነነቱ የተጠበቀ እና አካታች የሚዲያ ምህዳር መፍጠር የሚያስችሉ ፖሊሲዎች እና የሕግ ማዕቀፎች ማጠናከር የስብሰባው አበይት አጀንዳ ነው።
ማዕቀፎቹ በተለይም ሴቶች በሚሰሩባቸው የሚዲያ ተቋማት ፍትሃዊ ውክልናን እንዲያረጋግጡ ማድረግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ምክክር እንደሚደረግ የአፍሪካ ህብረት መረጃ ያመለክታል።
ቴክኖሎጂ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ዲጂታል አማራጮች እኩልነት የሚያንጸባርቁ ትርክቶችን ከመቅረጽ አንጻር ያላቸው ሚና ሌላኛው የትኩረት አጀንዳ ነው።
አዲስ የአፍሪካ ሴቶች በሚዲያ የፖሊሲ መግለጫ ይፋ እንደሚሆንና የጋራ አቋም የተያዘባቸውን ጉዳዮች ተፈጻሚነት የሚከታተል ቡድን እንደሚቋቋምም ተመላክቷል።
ኮንፍረንሱ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ምክረ ሀሳቦች መሰረት የሚጥል፣ የተጠያቂነት ማዕቀፎችን ማስፋት እና በባለድርሻ አካላት መካከል ጠንካራ ትብብርን ለመፍጠር እንደሚያስችል ተገልጿል።
ሁነቱ በአፍሪካ ሚዲያ የሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎ ማሳደግ እንዲሁም ተደማጭነት የመጨመር ጥረት አካል መሆኑን ህብረቱ ያስታወቀ ሲሆን ኮንፍረንሱ እስከ ነገ ይቆያል።